አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በዳኛ ውሳኔ ላይ በሰጡት አስተያየት ቅጣት ሊተላለፍባቸው ይችላል

አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ከጅማ አባ ጅፈር ሽንፈት በኋላ በዕለቱ ዳኛ ላይ በሰነዘሩት አስተያየት የጨዋታው ኮሚሽነር ያቀረቡትን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ትላንት ጉዳዮን የተመለከተው የዲሲፒሊን ኮሚቴ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ደደቢት ከ ጅማ አባጅፈር ባገናኘው ጨዋታ እንግዶቹ ደደቢትን 2-1 አሸንፈው መውታታቸው ይታወሳል። አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ” በዳኝነት ተሸንፈን ወጥተናል፡፡ የእኛ ሀገር እግርኳስ የሚገድሉት ዳኞች ናቸው። የተሰጠው ቀይ ካርድ ከመነሻው ጀምሮ ደደቢትን ለመግደል የተፈለገ ሴራ ነው ብዬ የማስበው፡፡ ›› ማለታቸው ከጨዋታው ውጤት በላይ የብዙ ስፖርት ባለሙያዎች እና የስፖርት አፍቃርያን መነጋገርያ እርስ ሆኖ ቆይቷል።

የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በሰጡት አስተያየት ዙርያ ትላንት ስብሰባ የተቀመጠ ሲሆን በጉዳዩ ዙርያ የጨዋታው ኮምሽነር የቀረበለትን ሪፖርት ከተመለከተ በኋላ ውሰኔ ይሰጣል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ውሳኔ ለመስጠት ደጋፊ ሰነድ እንዲቀርብለት እንደፈለገ እና ሰነዱን መርምሮ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ጥፋተኛ ሆነው ካገኘ ከበድ ያለ ቅጣት ለማስተላለፍ ለየካቲት 1 ቀጠሮ ሰጥቶ ወጥቷል።

አሰልጣኝ ንጉሴ በሰጡት አሰትያየት ዙርያ የክለቡ አቋም ምን እንደሆነ የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አምደመስቀል ለሶከር ኢትዮጵያ የሚከተለውን ብለዋል፡፡ ‹‹ አሰልጣኝ ንጉሴ የሰጠው አስተያየት የክለቡ አቋም እንዳልሆነ ለማሳወቅ እንወዳለን። ሆን ተብሎ ደደቢት ላይ የተሰራብን ሴራ አለ ብለን አናምንም፡፡ ለዳኞቻችን ትልቅ ክብር አለን፡፡ አልቢትር ኃይለየሱስ ባዘዘው ትልቅ ስብዕና ያለው ሙያውን የሚያከብር እና ትልቅ አድናቆት ከምንሰጣቸው ዳኞች መካከል አንዱ ነው። ይሄንንም ደውለን ለራሱ ለኃይለየሱስ ባዘዘው በሚገባ ገልፀንለታል። አሰልጣኝ ንጉሴም ከዚህ በኋላ እንደነዚህ ካሉ ስሜታዊ መግለጫዎች እንዲቆጠቡ አሳስበናል›› ብለዋል ።

በዚህ ዙርያ አሰልጣኝ ንጉሴን ደስታ ከመግለጫው በኋላ ያላቸውን ሀሳብ ለማስተናገድ ያደረግነው ጥረት ያልተሳካ ሲሆን የኢትዮዽያ ዳኞች ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው ጉዳዩን አስመልክቶ ያላቸውን ሀሳብ ጠይቀን ጉዳዩን ከመስማት ውጭ ምንም መረጃ እንደሌላቸውና ውሳኔ ሰጪው የዲሲፒሊን ኮሚቴ የሚወስነውን ውሳኔ ከሰሙ በኋላ መረጃ እንዲሰጡ ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *