​ሪፖርት | መቐለ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

የ15ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በተካሄደ ብቸኛ ጨዋታ ሲጀመር መቐለ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ ያለ ግብ በአቻ ወጤት ተለያይቷል።

ባለሜዳዎቹ መቀለ ከተማዎች በመጀመርያዎቹ 10 ደቂቃዎች ከረጅም ርቀት በሚጣሉ ኳሶች የቡና የተከላካይ ክፍልን ለመፈተን ቢሞክሩም ግልፅ የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም። በ1ደቂቃ ላይ ያሬድ ከበደ የቡና ተጫዋቾች መዘናጋት ተመልክቶ በረጅሙ ለአማኑኤል ያቀበለው ኳስ ሀሪሰን ቀድሞ ያወጣው ኳስ የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

አስደንጋጭ የግብ ሙከራ ባልታየበት የመጀመርያ አጋማሽ በ11ኛው ደቂቃ ላይ አንተነህ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ አማኑኤል በግንባሩ ገጭቶ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ የወጣበት በመቐለ በኩል ፣ በ15ኛው ደቂቃ ላይ ከ ፍ.ቅ.ም ክልል ውጭ በረጅሙ የመታውን ኳስ ኢቮኖ በቀላሉ የያዘበት በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሊጠቀሱ የሚችሉ ሙከራዎች ናቸው።

ለአጥቂዎች በሚሻገሩ ያልተሳኩ ረጃጅም ኳሶች  ታጅቦ በቀጠለው የመጀመርያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም እምብዛም ክፍተት የማይሰጠው የመቐለ የተከላካይ ክፍልን ማስከፈት ተስኗቸው ታይተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው የተሻለ የኳስ ፍሰት ቢታይበትም ሁለቱም ቡድኖች በተደራጀ ሁኔታ ወደተጋጣሚ የግብ ክልል ዘልቀው በመግባት ረገድ ግን ለውጥ ሳይታይበት ቀርቷል። በ52ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል አድሃኖም በረጅሙ ያሻማውን ኳስ ያሬድ ከበደ ሞክሮ ኢላማው ሳይጠብቅ ወደ ውጭ የወጣበት ሙከራም በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ 30 ደቂቃዎች ውስጥ ብቸኛው ሊጠቀስ የሚችል ሙከራ ነበር።

በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳትና የሰአት ማባከን ትዕይንቶች ታጅቦ በቀጠለው ጨዋታ መቐለ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች የተሻሉ የጎል ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በ76ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው መድሃኔ ታደሰ ለቢስማርክ አቀብሎት ጋናዊው አጥቂ ሲመታው ወንድይፍራው ተደርቦ ያወጣበት እንዲሁም በ81ኛው ደቂቃ አማኑኤል ከሳጥን ጠርዝ መትቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ሙከራዎች በመደበኛው ክፍለ ጊዜ የታዩ ሲሆን በጭማሪው 3ኛ ደቂቃ ላይ አመለ ሚልኪያስ ከመድሃኔ የተሻማውን የመዓዝን ምት በግንባሩ ገጭቶ ሃሪሰን የመለሰበት ሙከራዎች መቐለ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ለፈጠረው ጫና ማሳያዎች ነበሩ።

ጨዋታው ያለ ጎል በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ መቐለ ከተማ ከመሪው ደደቢት ነጥቡን እኩል አድርሶ በግብ ልዩነት ተበልጦ ባለበት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲረጋ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 19 አድርሶ በ6ኛ ደረጃ መቀመጥ ችሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *