​የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን 9ኛ ሳምንት ውሎ

9ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ጨዋታዎች ዛሬ አዲስ አበባና ክልል ከተሞች ላይ ተካሂደዋል። የሴቶች እግርኳስ የፉክክር ደረጃ ከፍ ማለቱ በታየበት በዚህ ሳምንት ሶስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መከላከያ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ሰብስበዋል። የጨዋታዎቹን ዝርዝር እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 0-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

(በዳዊት ጸሃዬ)

ቅድሚያ በ9 ሰአት በአዲስአበባ ስታዲየም የተገናኙት ሊጉን ከመሪው ደደቢት በ6 ነጥብ አንሶ በ14 ነጥብ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በ7 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
በመሀል ሜዳ ላይ የተገደቡ የጎንዮሽና የኃልዮሽ ቅብብሎች የበዙበት እንዲሁም የጠሩ የግብ እድሎች ያልነበረበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከቋሙ ኳሶች በቀጥታ ወደ ግብ ከተሞከሩ እንዲሁም በጭንቅላት ተገጭተው ከተሞከሩ ሙከራዎች በስተቀር በክፍት ጨዋታ ምንም አይነት የግብ ሙከራ አልተስተናገደበትም፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሶስት አጋጣሚዎች በመሀል ተከላካያቸው መሠሉ አበራ ከቋሙ ኳሶች በቀጥታ ወደ ግብ በላከቻቸው ኳሶች የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳን ግብጠባቂ ትእግስት አበራን መፈተን ችለዋል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በማጥቃቱ በኩል ተዳክመው የተስተዋሉት ንግድ ባንኮች በ21ኛው ደቂቃ ላይ ንግድ የካቲት መንግስቱን አስወጥተው በቅድስት ቦጋለ በመተካት የነበረባቸውን የመሀል ሜዳ የፈጠራ ክፍተት ለመሙላት ያደረጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ አልነበረም፡፡

ምንም አይነት የግብ ሙከራ ማድረግ የተሳናቸው ንግድ ባንኮች የመጀመሪያውን ሙከራ ለማድረግ 37ያክል ደቂቃዎችን ለመጠበቅ ተገደው ነበር ፤ በ37ተኛው ደቂቃ ህይወት ዳንጊሶ ያሻማችውን የቅጣት ምት በጊዮርጊስ ተከላካዮች ሲመለስ ታሪኳ ደቢሶ ወደ ግብ የላከችውን ኳስ የጊዮርጊስ ተከላካዮች ተረባርበው ሊያድኑባት ችለዋል፡፡
በጨዋታው ሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው ሁሉ ቀዝቀዝ ብሎ ተካሂዷል፤ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በነበሩት 20 ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የማሸነፍ ፍላጎት በማሳየት መጫወት ችለዋል፡፡ በተለይ በ64ኛው እና በ77ኛው ደቂቃ ረሂማ ዘርጋውና ፅዮን እስጢፋኖስ በግንባር በመግጨት ወደ ግብ የላኳቸው ኳሶች ተጠቃሾች ነበሩ፡፡ በአንጻሩ በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል በ84ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂያቸው ብዙሀየሁ ታደሠ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ግብጠባቂ ትእግስት አበራ ጋር ተገናኝታ ትእግስት ፈጥና ወታ የያዘችባት ኳስ በጣም አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡

ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ንግድ ባንክ አሁንም ከመሪው ደደቢት በአንድ ጨዋታ አንሶ በ15 ነጥብ በሁለተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ልዩነቱን የማጥበብ እድሉን ሲያመክን ሲችል ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን ወደ 8 በማሳደግ አሁንም በ8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 ድሬዳዋ ከተማ

(በዳዊት ፀሃዬ)

በመቀጠል በ11ሰአት የተገናኙት በ3 ነጥብ የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪክና በ9 ነጥብ በ6ተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ነበሩ በጨዋታውም ኤሌክትሪኮች 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ማስመዝገብ ችለዋል፡፡
በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል ገና በ7ኛው ደቂቃ የቀድሞዋ የሉሲዎቹ አምበል እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ድሬዳዋ ከተማን በአምበልነት እየመራች የምትገኘው ብዙሃን እንዳለ ባጋጠማት ጉዳት በሰናይት መኩሪያ ተቀይራ ለመውጣት ተገዳለች፡፡
ድሬዳዋ ከተማዎች በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል በፍጥነት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል ያብስራ ይርዳህ አስደናቂ ፍጥነቷን ተጠቅማ የኤሌክትሪክ ተከላካዮችን አልፋ ወደ ግብ የላከችውና የኤሌክትሪክ ተጫዋች ከግብ አፋፍ ላይ ካዳኑባት ኳስ በዘለለ ተጠቃሽ የግብ ሙከራ በመጀመሪያው አጋማሽ አልነበረም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ69ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረላትን ኳስ ተቆጣጥራ በግሩም ሁኔታ ማስቆጠር ችላለች። ከዚች ግብ መቆጠር በኃላ ድሬዳዋ ከተማች አቻ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በዚህ አጋማሽ በተለይ የድሬዳዋ ከተማዎች ጨዋታውን በመሩት አልቢትር ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ ተስተውሏል፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፉን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 6 በማሳደግ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ያላቸውን ተስፋ ሲያለመልሙ በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማ በ9 ነጥብ አሁንም በ6ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡

ሀዋሳ ከተማ 0-0 ሲዳማ ቡና

(በቴዎድሮስ ታከለ)

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ ያለምንም ግብ ጨዋታውን አጠናቋል። ሁለቱ ክለቦች ወትሮም ሲገናኙ በሜዳ ላይ ከሚታየው የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ባለፈ እልህ አስጨራሽ ፉክክር የሚያሳየን የነበረ ቢሆንም ዛሬ ግን እጅግ ቀዝቃዛ እና የወረደ የኳስ ፍሰትንም እና አነስተኛ የግብ ሙከራን ተመልክተናል። 23ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ ከቀኝ መስመር ያሻገረችላትን ኳስ ሳራ ኬዲ በግንባሯ ገጭታ ለጥቂት የወጣባት ሙከራ በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀስ የግብ እድል ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽም ተመሳሳይ እንቅስቃሴን ያስተዋልን ሲሆን ሁለቱም ክለቦች ይህ ነው የሚባል የጠራ የግብ እድልን መፍጠር አልቻሉም። በሁለተኛው  አጋማሽ ልትጠቀስ ምትችለው 71ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ ከማዕዘን ምት የተገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግቡ ስትሄድ የሲዳማዋ ግብ ጠባቂ ሚሪንዳ ጨመረ እንደምንም ያወጣችባት አጋጣሚ ብቸኛ ሙከራ ስትሆን ሲዳማዎች አብዛኛዎቹ ን ደቂቃዎች አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ተከላክለው ተጫውተዋል።

በ79ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማዋ የቀኝ መስመር ተከላካይ አይናለም አደሌ የሲዳማ ቡናዋ መስታወት ባልቻን በክርን ተማታለች በማለት ረዳት ዳኛው ለዋናው ዳኛ በመናገሯ በቀጥታ ቀይ ከሜዳ ወጥታለች። ከቀዩ በኃላም የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ተገቢ አይደለም በሚል ተቃውሟቸውን በማሰማት ለ7 ደቂቃወች ተቋርጦ ቢጀምርም ያለ ግብ ጨዋታው ተጠናቋል።

ሌሎች መርሀ ግብሮች

(በቴዎድሮስ ታከለ)

በ9ኛው ሳምንት ሌላኛው መርሀ ግብር ጠንካራው አዳማ ከተማ በሜዳው አበበ ቢቂላ ስቴዲየም መከላከያን ገጥሞ ሽንፈትን አስተናግዷል። በ13ኛው ደቂቃ ላይ በግራ የአዳማ የግብ መስመር እመቤት አዲሱ ያሻገረችላትን ኳስ ተከላካዮዋ ፋሲካ በቀለ በግንባሯ ገጭታ ግብ በማስቆጠር መከላከያን ቀዳሚ ስታደርግ በ17ኛው ደቂቃ ላይ መቅደስ ማሞ መሀል ለመሀል አሾልካ የሰጠቻትን ኳስ አይዳ ዑስማን በፈጣን ሩጫ አምልጣ ወደ ግብነት በመለወጥ አዳማን አቻ አድርጋለች። በ27ኛው ደቂቃ ላይ ሄለን ሰይፉ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት አክርራ በመምታት ባስቆጠረችው ጎል መከላከያን በድጋሚ ቀዳሚ ስታደርግ በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ 45ኛ ደቂቃ ላይ ሄለን ሰይፉ አመቻችታ የሰጠቻትን ኳስ የምስራች ላቀው ሶስተኛውን አክላ ጨዋታው በመከላከያ አሸናፊነት መጠናቀቁን ከአዳማ ባልደረቦቻችን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ዲላ ላይ የሊጉ መሪ ደደቢትን ያስተናገደውና ባለሜዳው ለትልልቆቹ ክለቦች ፈታኝ የሆነው ጌዲዮ ዲላ ቻምፒዮኖቹን ነጥብ አስጥሏል። በ47ኛ ደቂቃ በሻቱ ረጋሳ በእፀገነት ላይ በሰራችው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሎዛ አበራ አስቆጥራ ደደቢት መሪ ብታደርግም በ62ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲካ ንጉሴ የሰጠቻትን ኳስ ፈጣኗ አጥቂ ሳራ ነብሶ አስቆጥራ ጌዲዮ ዲላን ነጥብ አጋርታለች። ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ፍፁም የበላይነቱን ያሳየው ደደቢት በሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ መጋራቱ አስገራሚ ሆኗል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *