​ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ ወደ ዋንጫው ፉክክር የተመለሰበትን ድል አስመዝግቧል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ጨዋታ ዛሬም ሲቀጥል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ 4-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ዋንጫው ፉክክር ተመልሷል።

8 ሰዓት ላይ በተደረገው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ንግድ ባንኮች ከፍተኛ የጨዋታ የበላይነት የተስተዋለበት ሲሆን በአንፃራዊነት እንግዳዎቹ  በጨዋታው ተዳክመው ታይተዋል።ገና ጨዋታው እንደተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ በአይናለም አሳምነው አማካኝነት ንግድ ባንኮች ግብ ማስቆጠር የጀመሩ ሲሆን ጨዋታው እንደተጀመረ ግብ ያስተናገዱት ድሬዳዋዎች ተደናግጠው በተደጋጋሚ ኳሶችን ሲያበላሹ እና አላስፈላጊ ረዣዥም ኳሶችን ሲያበዙ ታይተዋል። ይህን ተከትሎም ከ8 ደቂቃዎች ቆይታ በኃላ ረሂማ ዘርጋው ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር የቡድኗን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች።

በግቦቹ ምክንያት ጨዋታው የቀለላቸው የሚመስሉት ንግድ ባንኮች ተረጋግተው በፈጣን የማጥቃት ሽግግር በተደጋጋሚ ወደ ድሬደዋዎች የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን በአንድ ሁለት ቅብብል ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ ከተጋጣሚያቸው ተሽለው ታይተዋል።

በ43ኛው ደቂቃ ንግድ ባንኮች የፍፁም ቅጣት ያገኙ ሲሆን ሽታዬ ሲሳይ ኳስ እና መረብን በማገናኘት ልዩነቱን ይበልጥ አስፍተዋለች። በዚህ አጋጣሚ ከአንድ አመት የጉዳት ቆይታ በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ ያስቆጠረችው ሽታዬ ሲሳይ የግብ አካውንቷን ከፍታለች።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የመጫወት ፍላጎት ያሳዩት ድሬዳዋዎች ጨዋታውን ለመቆጣጠር እና የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ የታየ ሲሆን በተቃራኒው በመከላከሉ ረገድ ተዳክመው ለተጋጣሚያቸው ተጋላጭ ሆነው ተደጋጋሚ የግብ ማግባት ሙከራ ሲደረግባቸው ታይቷል።

በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ጎል በማስቆጠር ድንቅ ብቃት እያሳየች የምትገኘው ረሂማ ዘርጋ ገና ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በ47ኛው ደቂቃ ለራሷ 2ኛ እንዲሁም ለቡድኗ 4ኛ ጎል ያስቆጠረች ሲሆን በአመቱም ያስቆጠረችውን የግብ ብዛት ወደ ስድስት ማሳደግ ችላለች።

ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ያሰቡ በሚመስል መልኩ የአጥቂ ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾችን ወደ ሜዳ ቀይረው ያስገቡት ንግድ ባንኮች ከዚህ በተሻለ በሰፊ የግብ ልዩነት ሊያሸንፉ የሚችሉበትን የግብ እድል በሽታዬ ሲሳይ እና ረሂማ ዘርጋው አማካኝነት ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *