ወልዋሎ ጸጋዬ ኪዳነማርያምን አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ

የፕሪምየር ሊጉ ክለብ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጸጋዬ ኪዳነማርያምን የክለቡ አዲስ አሰልጣኝ አድርጎ በዛሬው እለት ሾሟል። አሰልጣኙ ከአርባምንጭ ከተማ ከተሰናበቱ ከ 2 ወራት በኋላ ወደ ስራ ተመልሰዋል።

በመጀመርያ አመት የሊጉ ተሳትፎ ድንቅ አጀማመር ያደረገው ወልዋሎ ቀስ በቀስ መንሸራተቱን ተከትሎ ከአሰልጣኝ ብርሀኔ ገብረእግዚአብሔር ጋር መለያየቱ የሚታወስ ሲሆን የመጨረሻዎቹ ሶስት መርሀ ግብሮችን በምክትሉ ሀፍቶም ኪሮስ እየተመራ ወደ ሜዳ ገብቷል። ክለቡ ከሁለተኛው ዙር ጀምሮ የሚመራውን አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ሲንቀሳቀስ ቆይቶ በመጨረሻም አመሻሹ ላይ ጸጋዬ ኪዳነማርያምን በአንድ አመት ውል ለመቅጠር ከስምምነት ላይ ደርሷል።

አዲሱ የወልዋሎ አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማርያም ከ1996 ጀምሮ በፕሪምየር ሊጉ የማሰልጠን ልምድ ያላቸው ሲሆን በትራንስ ኢትዮጵያ ፣ ሐረር ቢራ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አርባምንጭ ከተማን አሰልጥነዋል። አሁን ደግሞ ካለፉት 10 ጨዋታዎች አንድ ብቻ ያሸነፈው ወልዋሎን ወደ መልካም መንገድ የመመለስ ፈተና ይጠብቃቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *