​ሪፖርት | መከላከያ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክቷል

በ12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሳይደረግ የቀረው የመከላከያ እና የመቐለ ከተማ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተደርጎ በባለሜዳዎቹ መከላከያዎች 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በቀዝቃዛማ አየር ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ ባለሜዳዎቹን ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ እንግዳዎቹን ደግሞ ከዋንጫ ፉክክሩ ላለመራቅ የተደረገ ጨዋታ ቢሆንም እምብዛም ጠንካራ ፉክክር እና የጎል ሙከራ ሳይታይበት ተጠናቋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ባለሜዳው መከላከያ ለአምስት አመታት ቡድኑን በአምበልነት ላገለገለው ሚካኤል ደስታ 13 ቁጥር ማልያውን በፍሬም በማድረግ ስጦታ ያበረከተለት ሲሆን ተጨዋቹም ስጦታውን ተቀብሎ ምስጋናውን አቅርቧል። በተመሳሳይ የመከላከያው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ እዚህ ደረጃ የደረስኩት በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳሕሌ ነው በሚል በቅጣት ቡድናቸውን ላልመሩት አሰልጣኝ ስጦታ ያበረከተ ሲሆን አሰልጣኙም ሽልማታቸውን በሚቀበሉበት ወቅት ከፍተኛ ድጋፍ ከተመልካች ተችሯቸዋል።

ፌደራል ዋና ዳኛ ሃብተሙ መንግስቴ በመሩት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መከላካያዎች 4ለ0 በተሸነፉበት የደደቢቱ ጨዋታ ሙሉቀን ደሳለኝን እና የተሻ ግዛውን በመቀየር አወል አብደላ እና ማራኪ ወርቁን በመጀመርያ አሰላለፍ ያስገቡ ሲሆን መቐለዎች ደግሞ ከቡናው ጨዋታ ዳንኤል አድሀኖምን በማስቀመጥ አሌክስ ተሰማን በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ አስገብተዋል።

10:20 በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መከላከያዎች በአንፃራዊነት ወደ ግብ በመድረስ ረገድ የተሻሉ ቢሆኑም በሊጉ አስተማማኝ የተከላካይ መስመር ያለው መቐለ ከተማን የኋላ ክፍል ለማስከፈት ተቸግረው ታይተዋል። ተመልካችን ቁጭ ብድግ የሚያስብል የሜዳ ላይ ፍክክር ያልተስተዋለበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቶሎ ቶሎ ኳስን የመነጣጠቅ እና መሃል ሜዳ ላይ ያተኮረ የጨዋታ አቀራረብ የታየ ሲሆን በአንፃራዊነት ባለሜዳዎቹ መከላከያዎች ከቆመ ኳስ የግብ ማግባት እድሎችን ሲፈጥሩ ነበር። ጨዋታው እንደተጀመረ በ6 ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ አወል አብደላ ብደላ ሞክሮት ለጥቂት የወጣበት ኳስም መከላከያን ገና በጊዜ ቀዳሚ ልታደርግ የምትችል የግብ ማግባት አጋጣሚ ነበረች።

በንፅፅር በመጀመሪያው አጋማሽ በትንሹም ቢሆን ተዳክመው የነበሩት መቐለዎች በተደጋጋሚ ወደ ግብ መድረስ ባይችሉም በ28 ደቂቃ በጨዋታው ብዙ ጥረቶችን በግሉ ሲያደርግ የነበረው  አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከአመለ ሚልኪያስ የተሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ የሞከረውን ኳስ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ በመቐለ በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ የተፈጠረች ብቸኛ የጠራች የግብ እድል ነበረች።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 6 ደቂቃዎች ሲቀሩት ከፍፁም ቅጣት ምት ውጪ አክርሮ የተመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፍሊፕ አቮኖ ሲተፋው ምንይሉ ወንድሙ አግኝቶት ወደ ግብ ቢመታውም አምና ቡድኑን ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየት ሊግ ካሳደጉ ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አሌክስ አውጥቶበታል። የመጀመርያው አጋማሽም ያለምንም ግብ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተሽለው ወደ ሜዳ የገቡት መቐለዎች ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያረጉት ጥረት የተሳካ ቢመስልም የጠራ የግብ ማግባት እድል ግን በተደጋጋሚ ሲፈጥሩ አልተስተዋለም። በ55 ደቂቃ ያሬድ ከበደ ከሃብታሙ ተከስተ የተሰነጠቀለትን ኳስ አማኑኤል ገ/ሚካኤል የተከላካዮቹን ትኩረት እና አቅጣጫ አስቀይሮለት ያገኛትን የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ወደ ውጪ የመታው ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ በመቐለዎች በኩል አስቆጪ አጋጣሚ ነበረች።

በ60ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ የነበረው ምንይሉ ወንድሙ ከቀኝ መስመር የግብ ጠባቂው ፍሊፕ አቮኖን አቋቋም ተመልክቶ የመታት ኳስ መረብ ላይ አርፋ ባለሜዳዎቹን 1ለ0 እንዲመሩ አስችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ በመልሶ ማጥቃት እና የፊት መስመራቸውን የተጨዋቾች ፍጥነት ለመጠቀም በሚመስል መልኩ ተደጋጋሚ ረጃጅም ኳሶችን ሲተገብሩ የነበሩት መቐለዎች በ85 ደቂቃ ከፍፁም ቅጣት ምት ውጪ ሚካኤል ደስታ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አቤል አውጥቶበት አማኑኤል አግኝቶት ወደ ግብ ቢመታውም አቤል  በድጋሚ ኳሷን አውጥቷታል። ጨዋታውም በዚህ መልኩ በመከላከያ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሊጉ በጠንካራ የመከላከል አቅሙ የሚታወቀው መቐለ ከተማ ዋና አሰልጣኙ ዮሀንስ ሳህሌን በቅጣት ምክንያት ቡድኑን ባልመሩበት ጨዋታ የውድድር አመቱን ሁለተኛ ሽንፈት ሲያስተናግድ ከሜዳው ውጪ ደግሞ ለመጀመርያ ጊዜ ሽንፈት ቀምሷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

የመከላከያ አሰልጣኝ ምንያምር ጸጋዬ

“ጨዋታው ጥሩ ነበር። መቐለዎች በተለይ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ሲሞክሩ ነበር። ነገር ግን ዛሬ እኛም ጥሩ ስለነበርን አሸንፈን ወጥተናል። ከደደቢቱ ሽንፈት በኋላ እንደመጫወታችን የተወሰነ ጫና ውስጥ ነበርን። ነገር ግን ጠንክረን በመጫወታችን እና ቶሎ ወደ አሸናፊነት ለመውጣት ስለምንፈልግ ወደ ድል ተመልሰናል። እርግጥ አንድ ጨዋታ ቀሪ አለን ፤ ግን በሁለተኛው ዙር እንደሌሎቹ ክለቦች የውጪ ሃገር ተጨዋቾችን ሳናስፈርም ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችን ከዚሁ ከሃገር ውስጥ በማስመጣት በሁለተኛ ዙር ተጠናክረን ለመቅረብ እንሞክራለን።”

የመቐለ ከተማ ም/አሰልጣኝ ጎይቶም ኃይለ

“ጨዋታው ጥሩ ነበር። ሙሉ 90 ደቂቃውን አጥቅተን ለመጫወት ሞክረን ነበር። ነገር ግን እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጎል ተቆጥሮብን ተሸንፈን ወተናል። እርግጥ ዛሬ የአጨራረስ ችግር ነበረብን ፤ የምናገኛቸውን የግብ ማግባት አጋጣሚ አልተጠቀምንም ነበር። ይሄ ደሞ ዋጋ አስከፍሎናል። ቡድናችን በመከላከሉ ጠንካራ ቡድን ነው። ዛሬ ግን በመዘናጋት ስህተት ሰርተን ተሸንፈናል።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *