​ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ድሬደዋ ከተማ | ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰሞኑን ተስተካካይ ጨዋታዎች እየተደረጉበት ሲገኙ ዛሬም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድሬደዋ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል። በጨዋታው ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች ለማንሳት ወደድን።

በ2009 የውድድር አመት መገባደጃ ላይ ላለመውረድ ይደረግ በነበረው ትግል ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ ከነበሩት ክለቦች ውስጥ የሚታወሱት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ድሬደዋ ከተማ ዘንድሮም ከደረጃው ግርጌ አልታጡም። የመጨረሻ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የዛሬውን ጨምሮ ሁለቱን ተስተካካይ ጨዋታዎቹን ተስፋ ያደርግ እንደሁ እንጂ ወቅታዊ አቋሙ አሁንም መሻሻልን አላሳየም። ቡድኑ በ15ኛው ሳምንት ከሲዳማ ይዞ የተመለሰው አንድ ነጥብ ካልሆነ በቀር ከዛ በፊት ከሜዳው ውጪም ሆነ ሜዳው ላይ የደረሱበት ተከታታይ ሽንፈቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው። በመጠኑ የተሻለ ጉዞ ያደረገ የሚገኘው ድሬደዋ ከተማ በበኩሉ በወልዋሎ ዓ.ዩ ላይ ያሳካው ድል እንዲሁም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ የተጋራበት ጨዋታ በቅርብ ሳምንታት ደረጃውን እንዲያሻሽል አግዘውታል። 

የዛሬው ጨዋታ ለድሬደዋ የመጨረሻው ተስተካካይ ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን ሙሉ ነጥብ ለማግኘት ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። ለኢትዮ ኤሌክትሪክም ቢሆን የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ የሜዳው ጨዋታ በመሆኑ ቡድኑ ካለበት የውጤት ቀውስ ለማገገም ዕድሉን የሚሞክርበት ይሆናል። በዚህ ጨዋታ ሌላው ትኩረት የሚስበው ጉዳይ የፌደራል ዳኛ አሰፋ መመደብ ነው። በክልል ጨዋታዎች ላይ በአወዛጋቢ ውሳኔዎች የሚታወቀው ይህ  ዳኛ በቀጣዮቹ ሰዐታት በምደባው ላይ ለውጥ ካልተደረገ በቀር ከሁለት አመታት በኃላ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም የሚመለስበት ጨዋታ ይሆናል።

የኢትዮ ኤሌክትሪኮቹ ዐወት ገ/ሚካኤል ፣ ሞገስ ታደሰ ፣ ቢኒያም አሰፋ ፣ ጥላሁን ወልዴ እና በሀይሉ ተሻገር በጉዳት ለዛሬው ጨዋታ የማይደርሱ ሲሆን የረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙትን ሀብታሙ ወልዴ ፣ ዘነበ ከበደ እና ሳምሶን አሰፋን ጨምሮ አናጋው ባደግ እና ሱራፌል ዳንኤል ደግሞ በድሬደዋ ከተማ በኩል በጉዳት ከቡድኑ ስብስብ ውጪ የሆኑ ተጨዋቾች ናቸው።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


የዛሬው የ11 ሰዐት ፍልሚያ በርካታ ግብ የሚቆጠርበት የተከላካይ ክፍልን ግብ የማስቆጠር ችግር ካለበት የአጥቂ መስመር የሚያገናኝ ነው። በውድድር ዘመኑ እስካሁን ሰባት ግቦች ያሉት ድሬደዋ ከተማ በወልዋሎ ላይ ካስቆጠራቸው ሁለት ግቦች በፊት የሊጉ ዝቅተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ነበር። ድሬደዋ በመከላከል ላይ የተመሰረተ ቡድን ሆኖ የውድድር ዘመኑን መጀመሩ በራሱ ለማጥቃት ቦታ መስጠት ከጀመረበት ጊዜ በኃላም የቡድን ውህደት ለማጥቃት የተመቸ በማድረግ በቶሎ ግቦችን በቀላሉ ማግኘት እንዳይችል አድርጎታል። ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ ካስቆጠራቸው አራት ግቦች መሀከል የሶስቱ ባለቤት የሆነው አትራም ኩዋሜ ወደ ግብ አስቆጣሪነቱ መመለሱ እንደፊት አጥቂ በራስ መተማመኑን ከፍ የሚያደርግለት ነው። በዛሬውም ጨዋታም በዚህ ተጨዋች እና ከጀርባው በሚኖሩት የማጥቃት ባህሪ ባላቸው አማካዮች መሀል የሚኖረው የቅብብል ስኬት ለብርቱካናማዎቹ ውጤት ማማር ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል። 

ምንም እንኳን መጨረሻ ደረጃ ላይ ይቀመጥ እንጂ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ከአብዛኛዎቹ የሊጉ ክለቦች የተሻለ ነው። ስድስት ክለቦች ብቻ ናቸው በ13 ጨዋታዎች 12 ግቦችን ካስቆጠረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተሻለ ጎል የማስቆጠር ንፃሬ ያላቸው። ሆኖም ቡድኑ ያስተናገዳቸው 21 ግቦች ደግሞ ከሁሉም ክለቦች በታች ያደርገዋል። የኃላ መስመር ድክመቱ እና ግብ በተቆጠረበት ቁጥር እየተከፈተ የሚሄደው የመከላከል አደረጃጀቱ በአራት ጨዋታዎች ሶስት ሶስት ግቦች እንዲቆጠሩበት አድርጓል።  የሚያስገርመው ሁሉም ጨዋታዎች አዲስ አበባ ላይ የተደረጉ ነበሩ። ይህም ቡድኑ በዛሬውም ጨዋታ በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት የሚያሳይ ነው። ባለፉት አራት ጨዋታዎች መቀዛቀዝ ያሳየው ግብ የማስቆጠር አቅምም ዛሬ ከተለመደው የነካሉሻ አልሀሰን የግል ጥረት ተላቆ በተደራጀ የማጥቃት ሂደት በመታገዝ መሻሻል ማሳየት የግድ ይለዋል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *