​“በክለቡ ታሪክ ውስጥ መካተት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ” አራፋት ጃኮ

በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ወላይታ ድቻ የዛንዚባሩን ዚማሞቶን በአጠቃላይ ውጤት አሸንፎ ወደ ቀጣይ የማጣሪያ ዙር ማለፍ ችሏል፡፡ ለሶዶው ክለብ ዛንዚባር ሲቲ እና ሀዋሳ ላይ በተደረጉት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው ቶጎዋዊው አጥቂ አረፋት ጃኮ ነው፡፡ ጃኮ ስለወላይታ ድቻ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ፣ ስለኮንፌድሬሸን ዋንጫ ጉዞ እና በድቻ እያሳለፈ ስላለው ግዜ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ረቡዕ እለት ያደረጋችሁትን ጨዋታ በድል ተወጥታችኃል፡፡ ግብም አስቆጥረሃል፡፡ በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር እየተሳተፈ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር በመቻልህ ምን ተሰማህ?

ሁላችንም ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ በመቻላችን ጥሩ ነገር እየተሰማን ነው፡፡ ጥሩ እንቅስቃሴ በሁለቱ ዙሮች ነበረን፡፡ አሰልጣኛችን (ዘነበ ፍስሃ) እየሰራ በሚገኘው ስራ ላመሰግነው እፈልጋለው፡፡ ለቡድኑ ጥሩ ነገር መስጠት እንደሚችል አውቃለው፡፡ ስለስሜቱ ለመናገር በጣም የተለየ ነው እና ጥሩ ነገር ይሰማኛል፡፡ ደጋፊዎቻችን በደንብ ይደግፉናል፡፡ እኛ እንድናሸነፍ የተቻላቸውን ሲያደርጉ ነበር፡፡ አሁን ላይ ለቀጣይ የሊግ እና የኮንፌድሬሸን ጨዋታዎች መዘጋጀት ነው ያለብን፡፡ አሰልጣኞቻችን፣ ደጋፊዋቻችን እና የክለቡ አስተዳደር ለሚያደርጉት ድጋፍ ማመሰግን እፈልጋለው፡፡ በጣም የተለየ ነገር ግን አይሰማኝም፡፡ ለእኔ ሌላ ግዜም እንዳስቆጠርኳቸው ግቦች ነው በውድድሩ ያስቆጠርኩትን ግብ የምመለከተው፡፡ የሚሰማኝ ስሜት እየተጫወትኩ እንዳለው እና ከጓደኞቼ ጋር እያሸነፍኩ እንደሆነ ነው፡፡ በክለቡ ታሪክ ውስጥ መካተት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ እንጂ የተለየ ስሜት አይሰማኝም፡፡

ቡድናችሁ ወደ ቀጣይ ዙር ቢያልፍም በእንቅስቃሴ ደረጃ ግን አሳማኝ አልነበረም፡፡ ትላንት የታየው እንቅስቃሴም እንዲሁ…

እውነት ለመናገር ከሜዳችን ውጪ ጥሩ ተጫውተናል፡፡ ትላንት ሀዋሳ ላይ ያደረግነው ጨዋታ ላይ ግን በሜዳችን መጫወት በሚገባን መልኩ አልተንቀሳቀስንም፡፡ ዚማሞቶ ሀዋሳ ላይ እንደዚህ ያለ ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳየናል ብለን ፈፅሞ አልጠበቅንም፡፡ እውነት ነው ጥሩ አልተጫወትንም፡፡ ዋናው እና ትልቁ ቁም ነገር ወደ ቀጣይ ዙር ማለፋችን ነው፡፡ ቢሆንም እንደትላንቱ ዓይነት ጨዋታ ከዛማሌክ ጋር የምናሳይ ከሆነ የምንተርፍ አይመስለኝም፡፡ አሰልጣኛችን እንቅስቃሴውን አይቷል ስለዚህም በዚህ ላይ ተመርኩዞ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ አስባለው፡፡

ኳሶችን ለማግኘት በጥልቀት ወደ ኃላ ስትመለስ ይታያል፡፡ በወላይታ ድቻ የማጥቃት ሽግግር ላይ በፍጥነት ኳሶች ስለማይደርሱ ትመለስ ነበር፡፡ ከጎንህ የሚያግዝህ ተጫዋች አለመኖሩም በትላንቱ ጨዋታ ላይ የታየ ነበር፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለህ?

እኔ እንደማስበው ቡድናችን ትንሽ ወደ ኃላ ተስቦ የሚጫወት ቡድን ነው፡፡ በመከላከል ላይ ትንሽ ያመዝናል፡፡ ግብ አስቀድመን ካስቆጠርን ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ፍላጎታችን የቀዘቀዘ ነው፡፡ መከላከልን እንመርጣለን፡፡ እኔም በዚህ ምክንያት ወደ ኃላ እየመጣሁ ኳስን ለማግኘት እና በመከላከሉ ማገዝ አለብኝ፡፡ በእርዳታ በኩል አዎ አጋዥ ያስፈልገኝ ነበር፡፡ ኳስ ወደ እኔ ሲመጣ በፍጥነት የመቀባበያ አማራጮችን የሚፈጥሩልኝ ተጫዋቾች በማጥቃቱ ወረዳ አይገኙም፡፡ ይህ ደግሞ ትንሽ እንድቸገር ሲያደርገኝ ነበር፡፡ ይህ የሚቀረፍ ችግር ነው፡፡

በንፅፅር ካሉት ተጫዋቾች የተሻለ የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ልምድ ያለህ አንተ ነህ፡፡ በቶጎ ብሄራዊ ቡድን፣ በእስራኤል እና ሩሲያ መጫወትህ ያስገኘልህ ልምድን ለሌሎች የቡድን አጋሮቾህ ለማጋራት ሞክረሃል?

የክለብ አጋሮቼን ምን ማድረግ እንዳለባቸሁ መናገር አይጠበቅብኝም፡፡ የምሰራውን ካዩ እነሱም ይከተላሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡ ይህን አርጉ ይህን አታርጉ ማለት የለብኝም፡፡ እኛ ከ17 ዓመት በታች ተጫዋቾች አይለንም፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ዚማሞቶ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መናገር ነበረብኝ፡፡ ከጨዋታ በፊትም ይህንኑ ማድረግ ስለነበረብኝ አድርጊያለው፡፡ አሁን ሁሉንም ነገር አይተዋል፡፡ ኢንተርናሽናል ጨዋታ ምን እንደሆነ አውቃዋለው የሚል ግምት አለኝ፡፡ ይህ የሊግ ጨዋታ አይደለም በጣም ይለያል፡፡

ቀጣይ ተጋጣሚችሁ ዛማሌክ ነው…

ዛማሌክ ትልቅ ቡድን ነው፡፡ እግርኳስ ስለትልቅ መሆን አይደለም፡፡ ነገሮች እየተለወጡ ነው፡፡ እኔ እንደማስበው ዛማሌክ አሁን ላይ ስም ብቻ ነው፡፡  እኛም ወላይታ ድቻ ነን፡፡ እኔ ዛማሌክን አልፈራም፡፡ ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች አሉብን፡፡ ምንአልባት እነሱ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ይዘዋል፡፡ እኛም የማሸነፍ ፍላጎት አለን፡፡ ይህ ፍላጎታችን ጥሩ እንድንጫወት የሚያደርገን ይመስለኛል፡፡ አሁን ላይ በኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላይ አለን። ከጨዋታዎቹ በኃላ አይታወቅም ፤ አሁን ግን በውድድሩ ውስጥ ነው ያለነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *