ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ወላይታ ድቻ

ተስተካካይ ጨዋታዎች እየተደረጉበት የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬም ጅማ ላይ የ14ኛ ሳምንት መርሀ ግብር የነበረውን ጨዋታ የሚያስተናግድ ይሆናል።  ጨዋታውን አስመልክተንም እነዚህን ነጥቦች አንስተናል።

ደካማ የውድድር አመታቸውን ቀልብሰው በሊጉ ወደ መልካም ጉዞ ከተመለሱ ክለቦች መሀከል ጅማ አባ ጅፋር እና ወላይታ ድቻ ተጠቃሽ ናቸው። አመቱን በድል በቀጣይ ቢጀምርም ሶስት ተከታታይ ሽንፈቶች ደርሰውበት የነበረው ጅማ አባ ጅፋር በቀጣዮቹ አስር ጨዋታዎች ግን የገጠመው አንድ ሽንፈት ብቻ ነበር። ከእነዚህ መሀል የሊጉን መሪ ደደቢትን አስገራሚ ጉዞ የገታበትን ጨዋታ ጨምሮ ግማሽ ያህሉን በድል አድራጊነት መወጣት ችሏል። ቡድኑ በተጠቀሱት ሳምንታት ሜዳው ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች አንድም ጊዜ እጅ አልሰጠም። በተመሳሳይ ከስድስተኛው ሳምንት ጀምሮ ሶስት ጨዋታዎችን በመደዳ የተሸነፈው ወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀን በኃላፊነት በመሾም በቀጣዮቹ አምስት ጨዋታዎች 11 ነጥቦችን ማሳካት ችሏል። ቡድኑ ከሜዳው ውጪ መከላከያን ከረታበት ጨዋታ ውጪ ሶስት ነጥብ ማሳካት የቻለበት ሌላ አጋጣሚን ባይፈጥርም ቢያንስ በእነዚህ ሳምንታት ሽንፈትን ማስወገድ ግን ችሏል። ዛሬ ጅማ ላይ በኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው መሪነት የሚደረገው ጨዋታም ከቡድኖቹ ወቅታዊ አቋም መነሻነት ብቻም ሳይሆን በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ሊያመጣላቸው ከሚችለው መሻሻል አንፃር ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል። 

ባለሜዳው ጅማ አባ ጅፋር በአዳማው ጨዋታ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ የወጣው አዳማ ሲሴኮን የማይጠቀም ሲሆን በአንፃሩ ከቅጣት የሚመለሰውን የሄኖክ አዱኛን አገልግሎት ያገኛል። ሌላው በቡድኑ ውስጥ የተሰማው መልካም ዜና ደግሞ የፊት አጥቂው ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ሜዳ መመለስ ሆኗል። በወላይታ ድቻ በኩል እርቅይሁን ተስፋዬ እና ፀጋዬ ብርሀኑ ከረዥም ጊዜ ጉዳታቸው ያላገገሙ ሲሆን በዛብህ መለዮም በጉዳት ወደ ጅማ እንዳልተጓዘ ሰምተናል። ከዚህ በተጨማሪም ኃይማኖት ወርቁ እና ጃኮ አራፋት የመጨረሻ ልምምዳቸውን አለመስራታቸውን ተከትሎ ለጨዋታው መድረሳቸውን አጠራጣሪ አድርጎታል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


የዛሬዎቹ ተጋጣሚዎች በውጤት ደረጃ ራሳቸውን ማሻሻላቸው ብቻ ሳይሆን በተጨዋቾች አጠቃቀማቸውም ተመሳሳይ ናቸው። በእጅጉ ተሻሽለው በታዩባቸው ጨዋታዎች የተረጋጋ እና በጉዳት ምክንያት ካልሆነ በቀር የማይለወጥ ምርጥ 11ን በመያዝ ጥሩ የሜዳ ላይ መግባባት ያለው ቡድን እያሳዩን ይገኛሉ። በዚህ መልኩ ጅማ አባ ጅፋር ሀሳቡን ማጥቃት ላይ ሲያደርግ እጅግ ፈጣን በሆነ እና በሁሉም አቅጣጫዎች የተመጣጠነ ጥቃትን በመሰንዘር ግቦችን የሚያስቆጥር ቡድን መገንባት ሲችል ወላይታ ድቻም የተሻለ አወቃቀርን በያዘው የመሀል ክፍሉ አማካይነት ለጃኮ አራፋት የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር ባለፈ በጥሩ የመከላከል ሽግግር የተጋጣሚን የአማካይ ክፍል መቆጣጠር የሚያስችልን መልክ ይዟል።

በዛሬው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በዋናነት አማካይ ክፍል ላይ የሚኖረው ፍልሚያ የጨዋታውን ሂደት የመወሰን አቅም ይኖረዋል። እዚህ ቦታ ላይ ብልጫ በሚወስድባቸው አጋጣሚዎች የጨዋታን ፍጥነት በመጨመር በቀላሉ የግብ ዕድልን የሚፈጥረው የዮናስ ገረመው እና ይሁን እንዳሻው ጥምረት ከተመስገን ገ/ኪዳን እና ሄኖክ ኢሳያስ የመስመር እንቅስቃሴ ጋር ተደምሮ የወላይታ ድቻን የአማካይ ክፍል መስበር ይጠበቅበታል። የጉዳት ዜናው ካላሳሳው በቀር በከፍተኛ የጨዋታ ትኩረት እና ታታሪነት ከተከላካይ አማካዩ ፊት እና ከጃኮ አራፋት ጀርባ የሚንቀሳቀሰው የወላይታ ድቻ የአማካይ ክፍልም ከሳጥን እስከ ሳጥን በሚንቀሳቀሰው  አብዱልሰመድ ዓሊ እየተመራ የጅማን የኳስ ቅብብሎችን በማቋረጥ ለራሱ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠሪያነት ለመጠቀም እንደሚንቀሳቀስ ይገመታል። ቡድኖቹ በራሳቸው ግብ ማስቆጠር ከሚችሉት አማካዮች በተጨማሪ ጥሩ የሆነ ዕድሎችን ወደ ግብ የመቀየር ንፃሬ ያላቸው አጥቂዎችን ከመያዛቸው አንፃር መሀል ሜዳ ላይ አሸናፊ መሆን ከቻሉ ኳስ እና መረብን ማገናኘት የሚቸግራቸው አይመስሉም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *