​ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር በኦኪኪ ጎሎች ታግዞ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል

በ14ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር ወላይታ ድቻን አስተናግዶ በኦኪኪ አፎላቢ ሁለት ግቦች በማሸነፍ። ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ማድረግ ችሏል።

ጨዋታው በስራ ቀን ቢደረግም እንደወትሮው የጅማ ስታድየም ከአፍ እስከ ገደፉ በደጋፊ ተሞልቶ ተስተውሏል። በጅማ አባ ጅፋር በኩል በአዳማው ጨዋታ ሁለት ቢጫ ካርድ የተመለከው የአዳማ ሲሴኮ የመሀል ተከላካይ ቦታ በአሚኑ ነስሩ የተሸፈነ ሲሆን ኦኪኪ አፎላቢን ከጉዳት ሔኖክ አዱኛን ከቅጣት መልስ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አካቶ እንዲሁም ለፍራኦል መንግስቱን እና ለኢብራሂም ከድርም ቅድሚያ በመስጠት  በ4-4-2 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምሯል። እንግዶቹ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ በካፍ ኮንፌዴሬሽን የመልስ ጨዋታ ዚማማኮን ከገጠመው ስብስብ በዛብህ መለዮን በበረከት ወልዴ በመተካት  በ4-1-4-1 አሰላለፍ ወደሜዳ ገብተዋል፡፡

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ በከተማው የሚገኘው ” ፋኖ ስፖርት” ባለፉት ጨዋታዎች በጅማ አባ ጅፋር በኩል ጥሩ መቀሳቀስ ለቻሉት አማካዮች ዮናስ ገረመው እና አሚኑ ነስሩ የወሩ ኮከብነታቸውን የሚያበስር የዋንጫ ሽልማት ከክቡር ከንቲባው እጅ  ተበርክቶላቸዋል።

የመጀመርያውን አጋማሽ በኦኪኪ አፍላቢ አማካይነት የጀመሩት ባለሜዳዎቹ  የጎል መከራ ማድረግ የጀመሩት ገና በመጀርያው ደቂቃ ኢብራሂም ከድር ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ኳስ የግቡን ቋሚ ታካ በወጣችበት አጋጣሚ ነው። በቀጣዮቹ  አምስት ደቂቃዎችም ሁለቱም ቡድኖች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን በድቻዎች በኩል ጃኮ አራፋት እና ዳግም በቀለ ኢላማቸውን ያልጠበቁ የግብ ሙከራዎች አድርገዋል።  ከነዚህ ሙከራዎች በኃላ ባለሜዳዎቹ ፍፁም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ የቻሉ ሲሆን በተደጋጋሚ የወላይታ ድቻ ተከላካዮችን መፈተን ችለዋል። በዚህም መነሻነት በ13ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር በሄኖክ አዱኛ የተሻገረውን ኳስ ሄኖክ ኢሳያስ በግንባሩ ሞክሮ በግቡ አግዳሚ  የወጣበት ኳስ በ15ቱ ደቂቃዎች ውስጥ ከተመለከትናቸው ሙከራዎች የሚጠቀስ ነው።

ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ጨዋታው ግብ ያስተናገደ ሲሆን በጥሩ ቅብብል ከሄኖክ አዱኛ የተሻገረውን ኳስ ኦኪኪ አፍላቢ በግንባሩ በመግጨት ነበር ኳስና መረብን ያገናኘው። ከግቡ መቆጠር በኃላ ድቻዎች በይበልጥ ተቀዛቅዘው አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ በራሳቸው የሜዳ ክልል በመቅረት ብልጫ ተወስዶባቸው እና አፈግፍገው ለመጫወት ተገደዋል። በዚህም ምክንያት ጅማዎች ተጨማሪ ጎል አያስቆጥሩ እንጂ በእለቱ ጥሩ ሲቀሳቀስ በዋለው ኦኪኪ አፍላቢ በኩል በ21ኛው ፣ 32ኛው እና 38ኛው ደቂቃዎች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በተቃራኒው ድቻዎች እንደ ቡድን ጥሩ ነበሩ ለማለት ያስቸግራል። አጥቂው ጃኮ አረፋት ብቻውን ተነጥሎ በተጋጣሚ ተከላካዮች ለመሸፈን የተገደደ ሲሆን የሚላኩለት ረዣዥም የአየር ላይ ኳሶችን ለማሸነፍም ተቸግሮ ታይቷል። በመሆኑም የጦና ንቦቹ በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ወደ  እረፍት አምርተዋል ።

ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር በኳስ ቁጥጥር ተሽለው የቀረቡት ወላይታ ድቻዎች የጎል ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ ነበሩ። ጃኮ አረፋት በ55ኛው ደቂቃ ወደግብ የሞከረውን ኳስ ዳንኤል አጄይ ይዞበታል። በጅማ አባጅፋር በኩል በተደጋጋሚ በቀኝ እና በግራ መስመር የሚያደርጓቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ እንዲሁም መሀል ሜዳ ላይ የዮናስ ገረመውና ይሁን እንዳሻው ጥምረት የሚደነቅ የነበረ ሲሆን ለተመስገን ገ/ኪዳንና ለኦኪኪ የሚላኩት ረጃጅም ኳሶች ድቻዎች ላይ ጫና መፍጠር ችለዋል። ለዚህም ማሳያ በ62ኛው እና 68ኛው ደቂቃ በተመስገንና በኦኪኪ አማካኝነት ያደረጓቸው ለግብ የቀረቡ አስደንጋጭ ሙከራዎች ናቸው።

በ72ኛው ደቂቃ ከማእዘን ምት የተሻማውን ኳስ ድቻዎች በአግባቡ ከግብ ክልላቸው ማራቅ ባለመቻላቸው ኦኪኪ አግኝቶ ወደ ግብነት በመቀየር ለቡድኑ ሁለተኛውን ለራሱ ደግሞ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ዘጠነኛ ግቡን በማስቆጠር የከፍተኛ ግብ አግቢነት ጣምራ መሪ መሆን ችሏል።
ከዚህች ግብ መቆጠር በኃላ ድቻዎች በሦስት ደቂቃ ውስጥ ጃኮ አረፋት ከ ዳንኤል አጄ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የተመለሰበትን ኳስ ዳግም በቀለ በ75 ኛው ደቂቃ በማስቆጠር የጎል ልዩነቱን መልሶ ማጥበብ ቢችልም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በባለሜዳዎቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱ ጅማ አባጅፋርን በ25 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጠው በአሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ ስር የመጀመርያ ሽንፈቱን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ በ16 ነጥቦች በነበረበት 9ኛ ደረጃ ረግቷል።

የአሰልጣኞች አሰተያየት 

የጅማ አባጅፋር አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ 

” አሸንፈን ወደ መሪዎች ለመጠጋት ያደረግነው ጥረት ተሳክቶልን መጠጋት ችለናል። በቡድኔ አጨዋወት ብዙም ደስተኛ ባልሆንም አሸንፈን መውጣታችን ጥሩ ነው። ከእቅዳችንም አኳያ የመጀመርያው ዙር ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው ማለት ይቻላል። በሁለተኛው ዙር ከጉዳት የተመለሱ ተጫዋቾችን እንዲሁም በተወሰነ መልኩ በአዲስ ተጫዋቾች ተጠናክረን ለመቅረብ እንሞክራለን።

የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ

 

በጨዋታው ጥሩ አልነበርንም። ከኮንፌዴሬሽን ጨዋታ እንደመምጣታችን በጨዋታ መደራረብ እና በጉዳት ምክንያት ተዳክመናል። ጅማዎችም ጥሩ በመንቀሳቀሳቸው አሸንፈዋል። ለቀጣይ ላለብን የኮንፌዴሬሽን ጨዋታና ለሁለተኛው ዙር ተጠናክረን እንቀርባለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *