​ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዲያ ከ መከላከያ

የ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሀ ግብር የነበረው የወልዲያ እና የመከላከያ ጨዋታ በተስተካካይነት ተይዞ ቆይቶ ዛሬ 9 ሰዐት ላይ እንደሚደረግ ይጠበቃል። ጨዋታውን አስመልክተንም በቅድመ ዳሰሳችን ተከታዮቹን ነጥቦች  አንስተናል። 

ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ከቻን መልስ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ይህ ጨዋታ ለመከላከያ የመጀመሪያ ዙር  የመጨረሻው ጨዋታ ሲሆን ወልዲያም ተስተካካይ ጨዋታዎቹን የሚያጋምስበት ይሆናል። አሁንም በሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኙት ወልዲያዎች ከአንድ ወር  በላይ ከሆነ ቆይታ በኃላ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ሜዳቸው አቻ ሲለያዩ ከ5 ጨዋታዎች በኃላ በ9ኛው ሳምንት ወደ ተገኘው የአርባምንጩ ድል መመለስ ሳይችሉ ቀርተዋል። ስማቸው ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር በስፋት እየተነሳ የሚገኘው ሰመያዊ እና ነጭ ለባሾቹ አርባምንጩ ድል በኃላ ባደረጓቸው 5 ጨዋታዎች ማሳካት የቻሉት ሁለት ነጥቦችን ብቻ መሆኑ ደግሞ የወቅታዊ አቋማቸው ጥሩ አለመሆንን ያሳያል። በተመሳሳይ ከአሸናፊነት ርቆ የሰነበተው መከላከያ በበኩሉ በሌላኛው ተስተካካይ ጨዋታው መቐለ ከተማን 1-0 በመርታት መጠነኛ መነቃቃት አሳይቷል። እስካሁን በአንድ ጨዋታ ከአንድ በላይ ግብ ማስቆጠር የተሳነው መከላከያ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ማለት የሚችል ሲሆን ወልዲያ ድል ከቀናው ደግሞ የመጨረሻ ደረጃውን ለአርባምንጭ ከተማ አስረክቦ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት ሙሉ ለሙሉ ከወራጅ ቀጠናው የሚወጣበትን ዕድል ይፈጥራል።  

ወልዲያ ተስፋሁን ሸጋውን ጨምሮ አሁንም በጉዳት ላይ የሚገኙትን  አዳሙ መሀመድ እና ሰለሞን ገ/መድህንን በዚህ ጨዋታ የማይጠቀም ሲሆን ትናንት ቀለል ያለ ልምምድ የሰራው ተስፋዬ አለባቸው የመግባት እና ያለመግባቱ ጉዳይም አለየለትም። በመከላከያ በኩል ደግሞ አዲሱ ተስፋዬ እና ቴውድሮስ በቀለ ከጉዳት ያላገገሙ ሲሆም ምንይሉ ወንድሙ እና ተመስገን ገ/ፃዲቅም በጉዳት ዝርዝሩ ውስጥ ተቀላቅለዋቸዋል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


በወልድያ በኩል የአማረ በቀለ ከቅጣት መመለስ እንዳለ ቢሆንም በቡድኑ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ይካተቱ የነበሩ ተጨዋቾች አለመኖር ለአሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ፈተና የሚሆን ይመስላል። በተለይም  ከወገብ በላይ ባለው የቡድኑ መዋቅር ውስጥ በማጥቃት ሂደት ላይ ወሳኝ የሆነው የተጨዋቾች ውህደት በድግግሞች የማይዳብር ከሆነ በሀከላቸው የሚኖረውን ጥምረት ውጤታማነት ይቀንሰዋል። በተመሳሳይ በመከላከያ በኩልም ቡድኑ እስካሁን ካስቆጠራቸው ስድስት ግቦች መሀከል የአምስቱ ባለቤት የሆነው ምንይሉ ወንድሙ አለመኖር የሚፈጥረው ክፍተት ቀላል የሚባል አይሆንም። ሌሎች የአማካይ ክፍል እና የፊት መስመር ተጨዋቾች በቋሚነት ወደ ግብ አስቆጣሪነት ካልተመለሱም መከላከያ ከግብ ፊት ያለው ደካማ ሪከርድ ውጤት እንዳያሳጣው ያሰጋል። 

እጅግ ወደ መሀል አጥቦ በመጫወት የሚታወቀው የመከላከያ የአማካይ ክፍል እንደ መቐለው አይነት በጥቂቱ የተሻሻለባቸው ጨዋታዎች ቢኖሩም አሁንም ብዙ መስተካከል ይጠበቅበታል። በዛሬውም ጨዋታ የግብ ዕድሎችን በብዛት ለመፍጠር በመስመር አማካዮቹ በኩል የሜዳውን ስፋት በአግባቡ የሚጠቀም ቡድንን ይዞ እንዲቀርብ ይጠበቅበታል። ወልድያዎችም በብሩክ ቃልቦሬ እና ምንያህል ተሾመ መሀከል በሚገኘው ቦታ ላይ መበራከታቸው የማይቀሩትን የተጋጣሚያቸው ተጨዋቾችን አልፈው ወደ አንዷለም ንጉሴ የመጨረሻ ኳሶችን ለማድረስ ሊቸገሩ የሚችሉ በመሆኑ በሁለቱ ክንፎች የምደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ቢያተኩሩ የሚሻል ይመስላል። በመሆኑም ጨዋታው መሀል ሜዳ ላይ ብዙ የቅብብል መቆራረጦች የሚገጥሙት እና የመስመር እንቅስቃሴዎች የተሻለ ክፍተትን የሚፈጥሩለት እንደሚሆን ይገመታል። 

የእርስ በእርስ ግንኙነት እውነታዎች

ተገናኙ – 4

ወልዲያ አሸነፈ – 1 (1 ጎል)

መከላከያ አሸነፈ – 3 (5 ጎሎች)

አቻ – 0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *