ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

አንድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ቀርቷቸው የነበሩት ሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በ15ኛው ሳምንት ሳይካሄድ በይደር ተይዞ የነበረውን ጨዋታቸውን ዛሬ ሀዋሳ ላይ ያደርጋሉ። ይህንን ጨዋታ በቅድመ ዳሰሳችን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ለአንድ ወር የሚዘልቀውን የ40ኛ አመት የምስረታ ክብረ በዓሉን በዚህ ጨዋታ ማክበር የሚጀምረው ሀዋሳ ከተማ ዘንድሮ ሜዳው ላይ ያደረጋቸውን የመጀመሪያ ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ካሸነፈ በኃላ ከድል ርቆ ሰንብቷል። ሀዋሳ ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ ሜዳው ላይ ካደረጋቸው እና በአቻ ውጤት ከተጠናቀቁት ሶስት ጨዋታዎች መሀከል ግብ ማስቆጠር የቻለው በአንዱ ላይ ብቻ ነበር። በተመሳሳይ ውጤት ማጣት ውስጥ በሚገኙት ቫስ ፒኒቶ የሚመራው እንግዳው ቅዱስ ጊዮርጊስም ጥር 9 ፋሲል ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ በኃላ  ሶስት ነጥብ ማሳካት ተስኖት ሰንብቷል። ባለፉት አራት ጨዋታዎችም ሜዳው ላይ ያደረጋቸውን ሶስቱን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ በሁለቱ ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቹ ቀድመው ግብ አስቆጥረውበታል። ቡድኑ ከሜዳው በወጣበት የመጨረሻ ጨዋታም ሶዶ ላይ በወላይታ ድቻ 2-1 መረታቱ የሚታወስ ነው። ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴውድሮስ ምትኩ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በአራተኛ ዳኝነት ከተመደበበት የኤፒአር እና አንሴ ሪዩኒየን ጨዋታ በኃላ በመሀል ዳኝነት የሚመራው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ለሀዋሳ ከተማ እስከ 8ኛ ደረጃ ከፍ የማለት ዕድልን የሚሰጠው ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስም ማሸነፍ ከቻለ ከደደቢት በሶስት ነጥቦች አንሶ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ይችላል።

ተክለማርያም ሻንቆን ከጉዳት እንዲሁም ፍሬው ሰለሞንን ከቅጣት መልስ የሚያገኙት ሀዋሳ ከተማዎች ከጉዳት ያገገመው ሳዲቅ ሴቾን መጠቀማቸው እርግጥ ያልሆነ ሲሆን አጥቂዎቹ ዳዊት ፍቃዱን እና ያቡን ዊሊያምንም በጉዳት ሳቢያ እንደማያሰልፉ ተሰምቷል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ ሳላሀዲን ሰይድ እና  አሜ መሀመድ ወደ ሀዋሳ ያተጓዙ ሲሆን ናትናኤል ዘለቀም ከረዥም ጊዜ ጉዳቱ አልተመለሰም።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታውን መሀል ሜዳ ላይ ኳስን በመቆጣጠር የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ለአጥቂዎች በመፍጠር ዕቅድ ላይ ተመስርተው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። ሆኖም በመሰል አቀራረብ ለረዥም ጊዜ የሚታወቀው ሀዋሳ ከተማ ሙሉ ለሙሉ በአጫጭር ቅብብሎች ላይ ተመስርቶ የተጋጣሚውን የኃላ ክፍል ለማስከፈት እንደሚጥር ሲጠበቅ በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥተኛ እና ተሻጋሪ ኳሶችን እንደ አስፈላጊነቱ እንደሚጠቀም ይገመታል። በተለይም በአዳማ ከተማው እና በደደቢቱ ጨዋታ ላይ እንዳስተዋልነው ቡድኑ ግብ ለማግኘት ከተቸገረ ወደ ሳጥን ውስጥ በረዥሙ ወደሚጣሉ ኳሶች ማዘንበሉ የማይቀር ነው። በዚህ ሂደትም እንደ ምንተስኖት አዳነ ያሉ የግንባር ኳሶችን የመግጨት ጥሩ ስኬት ያላቸው ተጨዋቾች ከሀዋሳ ከተማው የሲላ መሀመድ እና መሳይ ጳውሎስ ጥምረት ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ የሚጠበቅ ነው። 

በፍሬው ሰለሞን መመለስ ምክንያት ከመጀመሪያ አሰላለፍ ውጪ ካልሆነ በቀር ረዥም የእግር ኳስ ህይወቱን ያሳለፈበትን ክለብ በተቃራኒው የሚገጥመው ሙሉአለም ረጋሳ እና ታፈሰ ሰለሞን የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ለቡድኑ ውጤት ወሳኝ የሚሆንበት ጨዋታ ነው። የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት አማካዮች ከኳስ ውጭ የሚፈጥሩትን ከፍተኛ ጫና ተቋቁሞ ስኬታማ ቅብብሎችን በማድረግ እና ከመስመር አጥቂዎች ጋር ጥሩ ግንኙነትን በመፍጠር የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ሀዋሳዎች የአማካይ ክፍላቸው የበላይነት ያስፈልጋቸዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ከአማካይ መስመር የሚነሱ ኳሶች ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ጀርባ ደርሰው ወደ ንፁህ የግብ ዕድልነት እንዲቀየሩ የባለሜዳዎቹ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ከሙሉአለም ጎን ከሚኖሩት ቦታዎች በመነሳት ወደ ፊት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በጨዋታው ተጠባቂ ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እውነታዎች

ተገናኙ – 36

ሀዋሳ ከተማ አሸነፈ – 6 (27 ጎሎች)

ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸነፈ – 23 (64 ጎሎች)

አቻ – 7

የዛሬው መርሀ ግብር በ91 ድምር ግቦች በርካታ ጊዜ ኳስ እና መረብ ከሚገናኙባቸው የሊጉ ጨዋታዎች መሀከል አንዱ ነው።  በ1997 ቅዱስ ጊዮርጊስ 7-1 ያሸነፈበትን ጨዋታ ጨምሮ አብዛኞቹ ጎሎች አዲስ አበባ ላይ ሲቆጠሩ ሀዋሳ ላይ በተደረጉ 18 ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 9ድሎችን እና 23 ግቦችን ሲያስመዘግብ 5 ጊዜ ማሸነፍ የቻለው ሀዋሳ ከተማ 15 ግቦችን አስቆጥሯል። 4 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በታሪክ በሀዋሳ ሜዳ ላይ የበላይነቱን ቢያሳይም ከሚሊንየሙ ወዲህ ግን ሀዋሳ ከተማ በተሻለ ሁኔታ የሜዳውን አድቫንቴጅ እየተጠቀመ ይገኛል። ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናትም ሽንፈት አላስተናገደም።

ሀዋሳ እና ጊዮርጊስ እንደ 2007 እና 2008 የውድድር ዘመናት ሁሉ ዘንድሮም በመጨረሻ ዙር ተገናኝተዋል። በ2007 የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ የነበሩት ብራዚላዊው ኔይደር ዶ ሳንቶስ የተሰናበቱት በሀዋሳ 2-0 ከተሸነፉ በኋላ ነበር። ዛሬም የሁለቱም ክለቦች አሰልጣኞች በውጤት ማጣት ጫና ውስጥ ሆነው ነው ቡድናቸውን የሚመሩት። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የ2007ቱ ታሪክ ይደገም ይሆን ?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *