​የወላይታ ድቻዎቹ ተስፈኛ ወጣቶች በረከት ወልዴ እና ቸርነት ጉግሳ …

የወላይታ ድቻ  ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ዘጠኝ አመታት ከሶዶ እና አጎራባች ክልሎች የሚገኙ ታዳጊዎችን በየአመቱ በመመልመል በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ለሊጉ ማበርከት ችሏል። በዘንድሮ አመት ደግሞ ወደ ዋናው ቡድን ካደጉ ታዳጊ ተጨዋቾች መካከል ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን እያሳዩ የሚገኙ ሁለት ተጨዋቾች አሉ ፤ ቸርነት ጉግሳ እና በረከት ወልዴ። ሁለቱ ተጨዋቾች የአማካይ ስፍራ ተሰላፊዎች ሲሆኑ እድገታቸው ፈጣን ነው። ዘንድሮ ነው ከ17 አመት በታች ቡድኑ በቀጥታ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የቻሉት ። እነዚህ  ታዳጊዎች የመጫወት ዕድል ባገኙባቸው አጋጣሚ ሁሉ  የሚያሳዩት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ሆኖ አገኝተነዋል ። በዛሬውም የተስፈኞች አምዳችን ስለነዚህ ሁለት ተጨዋቾች እድገት እና አሁን ስለሚገኙበት ወቅታዊ ሁኔታ ፣ ወደፊትም ስለሚያስቡት ጉዞቸው ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር ቆይታ አድርገዋል። እኛም እንዲህ ባለ መልኩ አሰናድተን አቅርብነዋል። መልካም ቆይታ !

ዕድገታቹ ፣ የትውልድ አካባቢያቹ እና  እግርኳስ አጀማመራችሁ እንዴት እንደሆነ  ግለፁልኝ ?  


ቸርነት
: ትውልዴም እድገቴም ወላይታ ሶዶ ነው ። እግርኳስ ተጫዋች ለመሆን ምክንያት የሆኑኝ ደግሞ ወንድሞቼ ሽመክት ጉግሳ እና አንተነህ ጉግሳ ናቸው። እነሱ ጨዋታ ሲኖራቸው የእነሱን ትጥቅ በመያዝ አብያቸው ወደ ሜዳ በመሄድ ጨዋታቸውን በማየት የጀመረው የመጫወት ፍላጎቴ አድጎ በመቀጠል ከ13 አመት በታች ፕሮጀክት ገብቼ መጫወት ጀመርኩ። ከዛም አምና ከ17 አመት ቡድኑ ውስጥ በመግባት ተጫውቼ ዘንድሮ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ችያለው ። ዘንድሮ  ብዙ ጨዋታ ባላደርግም ባገኘሁት የመጫወት እድል የምችለውን አድርጌ እየወጣው እገኛለው። 


በረከት
፡ የእኔ ትውልድ በወላይታ አጎራባች ከተማ ከሆነችው አረካ ነው። በአካባቢያችን ብዙ ተጫዋቾች አሉ። አረካ ከተማ የሚባል ቡድን ሲጫወት እነሱን በማየት ነው ተጨዋች የመሆን ፍላጎት ያደረብኝ። በተለይ አባቴ ወልዴ ዋዛ ነው እንድጫወት ይገፋፋኝ የነበረው ። እንዲያውም የሆነ ጊዜ ጥሩ ስጫወት አይቶ እና በአጨዋወቴ ተደስቶ መቶ ብር አውጥቶ የሸለመኝን ጊዜ  አስታውሳለው። እሱ ነው እዚህ እንድደርስ የረዳኝ በዚህ አጋጣሚ አባቴን ከልብ አመሰግነዋለው ። ከዛ ቀጥዬ እዛው አረካ በአሰልጣኝ ሙሉአለም ቱሎማ በሚሰለጥን ቡድን ውስጥ ገብቼ እየተጫወትኩ አሁን የዋና ቡድናችን አሰልጣኝ በሆነው ዘነበ ፍስሀ አማካኝነት ወደ ወላይታ ድቻ ከ17 አመት በታች ቡድን ውስጥ ገብቼ መጫወት ቻልኩ።


ሁለታችሁም ከ17 አመት በታች ቡድን ውስጥ አምና አብራችሁ ተጫውታችኋል። እንዴት ነበር የአምና ቆይታቹ ?


ቸርነት
፡ መልካም ነበር። ያገኘነው ስልጠና ጥሩ ነበር ፤ ደስ የሚል ጊዜ ነበር ። ዘነበ ፍስሀ ጥሩ አድርጎ ያሰለጥነን ነበር። የእሱ ድጋፍ ነው እዚህ እንድንደርስ ያደረግን የአምናው ውድድራችንም ጥሩ ነበር። የጥሎ ማለፍ ዋንጫን አዳማ ላይ ማሸነፍ ችለናል።


በረከት
፡ አምና በደንብ ሰርተን ነበር ወደ ውድድር የገባነው። በጣም ጥሩ ስብስብ የነበረው ቡድን እና ኳስ የሚችሉ ተጫዋቾች የነበሩበት ነው ። የቡድኑ አምበል ሆኜ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ማንሳት የቻልኩበት ጥሩ ጊዜ ነበር ። አምና ባሳየነው ጥሩ እንቅስቃሴ ዘንድሮ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ችለናል ።


እድገታችሁ ፈጣን ነው። ከ17 አመት በታች ቡድን ነው በቀጥታ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የቻላችሁት ። በፍጥነት ወደ ዋናው ቡድን እና ወደ ሊግ ውድድር ያደረጋችሁት ሽግግር አልከበዳችሁም?


ቸርነት
፡ በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ መጫወት ከባዱ ነገር ነው። ዋናው ነገር ከሰራህ እና አሰልጣኝ የሚነግርህን ከሰማህ የሚከብድ ነገር የለም። ታዳጊዎች በመሆናችን ትንሽ የሚከብደን ጉልበት ነው። ሊጉ የጉልበት ጨዋታ ያመዝንበታል እኛ ደግሞ እንደምታየው ብዙም ጉልበት የለንም ። ከየትኛው ክለብ የሚመጡ ታዳጊዎች በጣም አቅም ያላቸው ኳስ መጫወት የሚችሉ ቢሆኑም ግን ትንሽ እየከበደን ያለው ጉልበት ብቻ ነው። 


በረከት
፡ በኔ እምነት በዚህ ምድር ላይ የሚከብድ ነገር አለ ብዬ አላስብም ። ሁሉም ነገር ቀላል ነው ። ከአንተ የሚጠበቀው ጠንክሮ መስራት ነው ። አሁን ያለንበት ደረጃ ገና ነው ፤ ብዙ የሚቀረን ነገር አለ ። ሆኖም የሚከብደን ነገር የለም። ወደ ሜዳ ገብተን ስናየው ሁሉም ቀላል ነው ።

በረከት በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታ ላይ ከዚማሞቶ ጋር በደርሶ መልስ ጨዋታ ላይ ተቀይረህ በመግባት ተጫውተሀል። የኢንተርናሽናል ጨዋታም ልምድ እያገኘህ ነው ። እስቲ ስለዚህ ነገር አጫውተኝ?

በረከት
: ሁሉም ነገር ስታየው ቀላል ይሆናል ። እኔ በራሴ እችላለው ነው የምለው ፤ ምንም የሚከብድ ነገር የለም። እኛ ታዳጊዎች ከኢትዮጵያ  ወጥተን መጫወት እንችላለን ፤ አቅም አለን ። ኢንተርናሽናል ጨዋታ ማድረጌ ደስ ብሎኛል። ቀሎኝ ነው የተጫወትኩት ፤ ምንም የሚካበድ ነገር የለውም ። ከእኛ በምንም የማይሻሉ ናቸው ። አንድ ነገር ግን ተምሪያለው ፤ እሱም በጣም በፍላጎት ነው የሚጫወቱት። ይህ ከእነሱ የተማርኩት ነገር ነው ። ከዛ ውጭ ራሳችንን ዝቅ አናድረግ እንችላለን ብለን ራሳችንን ማሳማን ይገባናል ። 


ከዚህ በኋላ ብዙ ነገር ይጠበቅባቹሀል።  ምን ታስባላቹ?


ቸርነት
: ከዚህ በኋላ ነው በጣም ጠንክረን መስራት የሚገባን ጊዜ። በፍጥነት ወደ ዋናው ቡድን መግባታችን የመሰለፍ እድል አግኝተን መጫወታችን መነሳስተን ፈጥሮልናል። ከዚህ በኋላ ጠንክረን እንሰራለን ፤ እኔ ደግሞ እንደ ወንድሞቼ ትልቅ ተጨዋች መሆን እፈልጋለው። እስካሁን ይመኩሩኛል ያግዙኛል። ስለዚህ በቅርቡ የቡድኑ ቋሚ ተጫዋቾች እንሆናለን ብዬ አምናለው። በፕሪምየር ሊጉም አሸብርቀን እንደምንወጣ እርግጠኛ ነኝ።


በረከት
፡ እኔ ህልሜ እዚህ ኢትዮዽያ ውስጥ መጫወት ብቻ አይደለም ። ጀግና ተጨዋች ከሆንክ ከዚህ ወጥተህ በውጪ ሀገር መጫወት አለብህ ። የመጀመርያ ህልሜ ድቻ ውስጥ ገብቶ መጫወት ነበር። ይህ ደግሞ ተሳክቶልኛል። በቀጣይ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት አስባለው ። በዚህ ብቻ አላበቃም ከኢትዮዽያ ውጪ አልፌ እንደምሄድም አምናለው ። የኢትዮዽያን የወደፊት የእግርኳስ ደረጃ የሚያሳድጉ ብዙ ታዳጊዎች ይመጣሉ ።

ወደፊት ትልቅ ደረጃ ለመድረስ በስነምግባር ራሳችሁን በማነፅ ታይታቹ እንዳትጠፉ ምን ማድረግ አለብን ትላላቹ ?


ቸርነት
: የእግር ኳስ ዋና መርህ ዲሲፒሊን ነው ። ዲሲፒሊን ከሌለለህ ምንም ችሎታ ቢኖርህ ዋጋ የለውም። ችሎታህ ብቻ ምንም አይጠቅምህም ። ወላይታ ድቻ ደግሞ ከሁሉ በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ለዲሲፒሊን ነው። ለታላላቆች መታዘዝ እንዳለብን ነው እየተማርን ያደግነው። አሁን ትኩረታችን ትልቅ ተጫዋች መሆን ላይ ብቻ ነው ። 

በረከት ፡ መጀመርያ ፈጣሪን መያዝ እና ማመን ነው ። ይህን ካደረክ ለወላጆችህ መታዘዝ ትጀምራለህ። ራስህን በጥሩ ስነ ምግባር እያነፅክም ትሄዳለህ ። የሁሉም ነገር ውድቀት ትዕቢት ነው። ብዙዎች የሚጠፉት በዚህ ምክንያት ነው ። ያለ እድሜ ገንዘብ ሲመጣ ወደዚያው ነው የሚያመራቸው። እኔ በዚህ አላምንም። በፈጣሪ ስለማምን ታዛዥ ሆኜ ወደ ፊት ብዙ ነገር መስራት ስለማስብ ራሴን ካላስፈላጊ ባህሪ እጠብቃለው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *