​ሲዳማ ቡና ከአሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ ጋር ተለያየ

በውድድር ዘመኑ ደካማ አጀማመር ያደረገውና ቀስ በቀስ ራሱን አሻሽሎ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ከፍ ያለው ሲዳማ ቡና ዋና አሰልጣኙ አለማየሁ አባይነህ እና የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ዮሴፍ ዮሀንስ ጋር መለያየቱ ታውቋል።


በ2008 የውድድር ዘመን አጋማሽ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ተክተው የሲዳማ ቡና አስልጣኝ የሆኑት አለማየሁ አባይነህ አምና ቡድኑን ጥቂት ሳምንታት እስኪቀሩ ድረስ ቡድኑን ለሊጉ ዋንጫ ማፎካከር ቢችሉም ዘንድሮ የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ ጉዞ እያደረገ አለመሆኑን እና ከዮሴፍ ዮሀንስ ጋር በፈጠሩት ልዩነት በደጋፊዎች ዘንድ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ቆይተዋል። በመጨረሻም ትላንት ክለቡ ከአሰልጣኙ ጋር ለመለያየት ከውሳኔ ላይ መድረሱ ታውቋል። የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ሳሳሞ በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ብለዋል። ” የተሰናበተበት ምክንያት ውጤት ነው። የደጋፊዎች ተቃውሞ እና ከተጫዋቾች ጋር ያለው አለመግባባትም ለውሳኔያችን አስተዋፅኦ አድርጓል። ክለባችን ካወጣው ወጪ አንፃር ውጤት ይፈልጋል ፤ ስለዚህ በሒደት ውጤት የሚያመጣ አሰልጣኝ የምንቀጥር ይሆናል። ለጊዜው ግን ምክትሉ ዘረረዓይ ይቀጥላል”  ብለዋል።
አሰልጣኙ መልቀቂያቸውን ከክለቡ እንደወሰዱ የተነገረ ሲሆን ምክትል አሰልጣኙ ዘርዓይ ሙሉ በጊዜያዊነት ከዛሬ ጀምሮ ቡድኑን ልምምድ ማሰራት መጀመሩም ታውቋል። ሲዳማ ቡና ከዚህም በተጨማሪ ከአሰልጣኙ ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ የነበረው ዮሴፍ ዮሀንስንም ጭምር ማሰናበቱን ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የቀድሞው የአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ አማካይ አለማየሁ አባይነህ አርባምንጭ ከተማን ከ2004-2007 በዋና አሰልጣኝነት ሲመሩ ከ2008 ጀምሮ በሲዳማ ቡና በረዳትነት በኋላም በዋና አሰልጣኝነት ሰርተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *