​ድሬዳዋ ከተማ ከሁለት ተጫዋቾቹ ጋር ተለያየ

እንዳለፉት ሁለት አመታት ሁሉ ዘንድሮም ላለመውረድ እየተጫወተ የሚገኘው ድሬደዋ ከተማ በክረምቱ ወራት ከፍተኛ ሂሳብ በማውጣት ከመውረድ ስጋት የራቀ ቡድን ለመገንባት በማሰብ ብዛት ያላቸውን ተጨዋቾች ማምጣቱ ይታወሳል። ሆኖም እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ክለቡ በሊጉ በ15 ጨዋታዎች 13 ነጥብ በመያዝ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የመጀመርያውን ዙር አጠናቋል ።

ይህን ተከትሎም አሁን ከክለቡ አካባቢ ባገኘነው መረጃ መሰረት አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ከደረሳቸው ተጨዋቾች መካከል ከኬንያዊው ተከላካይ ሰንደይ ሙቱኩ እና ከዘካርያስ ፍቅሬ ጋር በስምምነት መለያየቱ ተሰምቷል ።

አምና በሲዳማ ቡና ጥሩ የውድድር አመት ያሳለፈው ሰንደይ ሙቱኩ  ድሬደዋ ከተማን ሲቀላቀል ብዙ ተስፋ የተጣለበት ቢሆንም እንደታሰበው የሚገባው አገልግሎት አለመስጠቱን ተከትሎ ከቡድኑ ጋር እንዲለያይ ሆኗል። ሌላው ከድሬደዋ ከተማ ጋር የተለያየው ዘካርያስ ፍቅሬ አምና በከፍተኛ ሊግ ለሀላባ ከተማ በመጫወት በውድድር አመቱ 21 ጎሎችን በማስቆጠር ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ አመቱን በኮከብነት ቢያጠናቅቅም ዘንድሮ ድሬደዋን ከነማ ተቀላቅሎ በተሰለፈባቸው ጥቂት ጨዋታዎች ግቦችን ማስቆጠር ሳይችል ከክለቡ ጋር ተለያይቷል።

በተያያዘ ዜናም ድሬደዋ ከተማ በሁለተኛው ዙር ለሚገጥመው ብርቱ ፈተና ራሱን አጠናክሮ ለመቅረብ አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ ለማስመጣት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ሰምተናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *