​ከፍተኛ ሊግ | ደቡብ ፖሊስ መሪነቱን ሲያጠናክር ሻሸመኔ ከሜዳው ውጪ አሸንፏል 

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የተስተካካይ መርሀ ግብሮች መካሄዳቸውን ቀጥለው ዛሬ ሁለት የምድብ ለ ጨዋታዎች ሲካሄዱ ደቡብ ፖሊስ አሁንም በሜዳው ግብ ማዝነቡን ሲቀጥል ሻሸመኔ ከተማ ወደ ድሬዳዋ ተጉዞ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክቷል።

በ09:00 ሀዋሳ ላይ ስልጤ ወራቤን ያስተናገደው ደቡብ ፖሊስ 4-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል። በእንቅስቃሴም ሆነ በግብ ሙከራ የበላይ የሆኑት ፖሊሶች በርካታ ያለቀላቸውን እድሎች ሲፈጥሩ ተስተውሏል። 8ኛው ደቂቃ ላይ አበባየሁ ዮሀንስ ያሻገራትን ኳስ ደስታ ገልገሎ በግንባሩ ሲገጭ የቀድምው የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ ጌቱ ተስፋዬ በአስደናቂ ሁኔታ አውጥቶበታል። በ18ኛው ደቂቃ አበባየው ዮሀንስ ፣ ቢኒያም አድማሱ እና ሚካኤል ለማ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ጠርዝ በመጠጋት ለአበባየሁ ተመቻችታ የመጣችን ኳስ አበባየሁ በቀጥታ መቷት ግብ ጠባቂው ጌቱ በድጋሚ አውጥቶበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኃላም ደቡብ ፓሊሶች አሁንም አበባየሁ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ አየለ ተስፋዬ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ የላይኛው ብረት መልሶበታል።

በ25ኛው ደቂቃ ብርሃኑ በቀለ ያሻማውን የማዕዘን ምት የቀድሞው የሀዲያ ሆሳዕና የግራ መስመር ተከላካይ አየለ ተስፋዬ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይሮ ደቡብ ፖሊስን ቀዳሚ አድርጓል። ከጎሉ በኋላ ደቡብ ፖሊሶች መሪነታቸውን ሊያሰፉ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች በአየለ ተስፋዬ እና ኤሪክ ሙራንዳ አማካኝነት መፍጠር ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር የመጀመሪያው አጋማሽ በደቡብ ፖሊስ 1-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ደቡብ ፖሊሶች በተጠናከረ መልኩ በልዩ የማጥቃት ኃይል ወደ ሜዳ ሲገቡ ስልጤ ወራቤዎች ምላሽ ለመስጠት ተቸግረው ውለዋል። 71ኛው ደቂቃ ላይ ኬኒያዊው አንጋፋ አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ በግሩም ሁኔታ የሰጠውን ኳስ ተጠቅሞ ሚካኤል ለማ ወደ ግብነት ለውጦ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ሲያደርግ በ76ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ክልል ሳጥን ውጭ በግምት 25 ሜትር ርቀት ላይ አማካዩ አበባየሁ ዮሀንስ 3ኛውን ጎል አስቆጥሯል። 84ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ማንያዘዋል ጉዳዩ በመስመር በኩል ሰብሮ በመግባት ያሻገረውን ኳስ ወጣቱ የመስመር አጥቂ ብሩክ ኤልያስ አስቆጥሮ ጨዋታው በደቡብ ፓሊስ 4-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ በውጤቱም መሰረት ደቡብ ፓሊስ በ23 ነጥቦች የምድብ ሁለት መሪነቱን አጠናክሯል።
10:00 ላይ በተደረገ ሌላ የተስተካካይ መርሀ ግብር ደካማ የውድድር ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው ሻሸመኔ ከተማ ወደ ድሬዳዋ አቅንቶ ናሽናል ሴሜንትን 2-1 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል።  በ36ኛው ደቂቃ በተስፋሁን ስለአለም እንዲሁም በ56ኛው ደቂቃ ጌታሁን ማሙዬ ባስቆጠራቸው ጎሎች ሻሸመኔዎች መሪ መሆን ሲችሉ ለናሽናል ሴሜንት ከመሸነፍ ያላዳነቻቸውን ጎል 85ኛው ደቂቃ ላይ በፈርአን ሰይድ አማካኝነት አግኝተዋል።

ወልቂጤ ላይ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የወልቂጤ ከተማ እና ነገሌ ቦረና ጨዋታ በድጋሚ ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *