ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዲያ ከ ደደቢት

ዛሬ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ወልዲያ ደደቢትን በሜዳው ያስተናግዳል። እንደተለመደው በቅድመ ዳሰሳችን ይህንኑ ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል። 

በፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ የመሀል ዳኝነት የሚካሄደው ይህ ጨዋታ ለወልዲያ ከነበቱት አራት ተስተካካይ ጨዋታዎች ሶስተኛው እና በሜዳው ደግሞ የመጨረሻው ሲሆን ደደቢትም የሊጉን የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎቹን የሚያጋባድድበት ይሆናል። አምና በሊጉ ሶስተኛው ዙር መልካ ቆሌ ላይ ተገናኝተው ያለግብ ጨዋታቸውን የጨረሱት ሁለቱ ክለቦች የዛሬውን ጨዋታ በአሸናፊነት ለመወጣት ብሩቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።  ከአንድ ወር በላይ ከውድድር ርቆ የቆየው ወልዲያ ተስተካካይ ጨዋታዎቹን በአግባቡ እየተጠቀመባቸው ይመስላል። ከኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ከመከላከያ ያገኛቸው አራት ነጥቦችም ከወራጅ ቀጠናው አውጥተውት 12ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አስችለውታል። ዛሬም ድል የሚቀናው ከሆነ በደረጃ ሰንጠረዡ ሽቅብ መውጣቱን በመቀጠል እስከ ስምንተኛ ደረጃ ድረስ መሄድ ያስችለዋል። በአንፃሩ ደደቢት የመጨረሻውን ጨዋታውን በድል በማጠናቀቅ  ከ30 ነጥቦች በላይ በመሰብሰብ የቻለ ብቸኛው ክለብ በመሆን ሊጉን በሰባት ነጥቦች ልዩነት ለመምራት እንደሚፋለም ይጠበቃል። 

አሁንም ድረስ ክለቡን ካልተቀላቀሉትን ታደለ ምህረቴ ፣ ፍፁም ገ/ማርያም እና ያሬድ ብርሀኑ በተጨማሪ የመከላከያው ጨዋታ ላይ የመጀመሪያ ተሰላፊዎች የነበሩት ብርሀኔ አንለይ እና ነጋ በላይ እንዲሁም ከዛም በፊት ያልነበሩት ሠለሞን ገ/መድህን እና ተስፋሁን ሸጋው በወልዲያ በኩል ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጨዋቾች ናቸው። ከዚህ ውጪ ተስፋዬ አለባቸው ለዚህ ጨዋታ መድረሱ አጠራጣሪ ሲሆን አዳሙ መሀመድም ለተጨማሪ ህክምና ወደ ጋና ማምራቱ ተሰምቷል። እንደተጋጣሚው ሁሉ ቁልፍ ተጨዋቾቹን የማይጠቀመው ደደቢት ከድር ኩሊባሊን በጉዳት ሲያጣ አስራት መገርሳ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ በተመለከታው ቀይ ካርድ ፣ ግብ ጠባቂው ክሌመንት አዞንቶም በዚሁ ጨዋታ ላይ በተመለከተው አምስተኛ ቢጫ ካርድ ይህ ጨዋታ ሲያልፋቸው ጌታነህ ከበደም ቅጣቱን ያልጨረሰ ሌላኛው ተጨዋች ነው።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


በወልዲያ በኩል የአንጋፋው አጥቂ አንዷለም ንጉሴ ጉዳይ ቀልብን የሚስብ ነው። አምና አስር ግቦችን በማስቆጠር ወልዲያ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በተመለሰበት አመት በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ አመቱን እንዲጨርስ ያደረገው አንዷለም ዘንድሮም አራተኛ ግቡ ላይ ደርሷል። ከነዚህ ግቦች መሀከል ደግሞ ሁለቱን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ማስቆጠሩ የተጨዋቹ ወቅታዊ አቋም ጥሩ መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም በዛሬው ጨዋታ ከመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርግስ ጋር ግብ ሳያስተናግድ ቢወጣም በከድር ኩሊባሊ እና ክሌመንት አዞንቶ አለመኖር እንደሚሳሳ ከሚጠበቀው የደደቢት የኃላ መስመር ጋር የሚያደርገውን ፍልሚያ ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል።

የጌታነህ ከበደን ቅጣት ተከትሎ ፊት ላይ የተፈጠረበትን ክፍተት በአኩዌር ቻሞ እና አቤል ያለው የሸፈነው ደደቢት ዛሬ ደግሞ የኃላ መስመሩ ላይ እና ጠንካራ የሚባለው የአማካይ ክፍል ጥምረቱ ላይ ለውጥ የሚያደርግ ይሆናል። በተለይ በአማካይ መስመሩ ፋሲካ አስፋው የአቤል እንዳለን እና የአብስራ ተስፋዬ ጥምረት ይበልጥ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ወሳኝ ሚና የነበረው አስራት መገርሳን ቦታን እንደሚሸፍን ይጠበቃል። የሶስትዮሽ ጥምረቱ ከመስመር አጥቂዎቹ ጋር በመሆን  ከብሩክ ቃልቦሬን እና ከሐብታሙ ሸዋለም ጀርባ ለመግባት በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርቶ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ደደቢት ለሚፈጥራቸው የጎል ማግባት አጋጣሚዎች ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። 

የእርስ በእርስ ግንዝኙነት እውነታዎች

ወልዲያ በፕሪምየር ሊግ ታሪኩ የመጀመሪያው ጨዋታው ከደደቢት ጋር የተደረገ ነበር ። 2007 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረገው ይህ ጨዋታ ወልዲያ እስካሁን ደደቢት ላይ በብቸኝነት ባስቆጠራት የአብይ በየነ ጎል ቢመራም ደደቢት 6-1 አሸንፎ ነበር። ይህን ጨምሮ እስካሁን በተጋኑኙባቸው 4 ጨዋታዎች 8 ግቦችን ያስቆጠረው ደደቢት ሶስት ጊዜ ባለድል ሲሆን ወልዲያ በሜዳው አንድ ጊዜ አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በቀር ማሸነፍ አልቻለም። 
                                       

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *