ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ | የጦና ንቦች ካይሮ ላይ ተናድፈዋል

ወላይታ ድቻ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ማጣርያ ታላቁ የግብፅ ክለብ ዛማሌክን በመጣል ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።

ወላይታ ድቻ ሀዋሳ ላይ የግብፁን ክለብ ካስተናገደበት ጨዋታ ቀኝ መስመር አማካይ ቦታ ላይ ዘላለም እያሱን በአመርላ ደልታታ ተክቶ ነበር ጨዋታውን የጀመረው። ያልተጠበቀ ሽንፈት ደርሶባቸው ወደ ግብፅ የተመለሱት ዛማሌኮች በበኩላቸው ሀዋሳ ላይ ግብ ያስቆጠረላቸውን ኢማድ ፋቲህን ጨምሮ የአራት ተጨዋቾች ለውጥ አድርገዋል። 

የካይሮው አልሳላም ስታድየም በጥቂት የዛማሌክ ደጋፊዎች እንዲሁም በካይሮ የሚገኙ የኢትዮጵያዊያን እና የወላይታ ድቻ ተጓዥ ደጋፊዎች አጀብ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን ጨዋታ አስተናግዷል። ዛማሌክ ከሜዳው ውጪ ሽንፈት አስተናግዶ የተመለሰ በመሆኑ በዚህ የመልስ ጨዋታ ምን አይነት ምላሽ ሊሰጥ ይችላል ? ወላይታ ድቻስ እንዴት ይቋቋመዋል ? የሚሉት ጥያቄዎች የጨዋታውን ግምት በእጅጉ ከፍ አድርገውት ነበር። የመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎችም ይህን ስጋት ያመላከቱ ነበሩ። በ2ኛው ደቂቃ የግራ መስመር ተከላካዩ ናሩፍ የሱፍ ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን ገረመው ጨርፎት አደጋ ከመፍጠሩ በፊት ተስፉ ኤልያስ ደርሶ ተቆጣጥሮታል። 

ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ይዘው ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ዛማሌኮች 7ኛው ደቂቃ ላይ በመሀመድ አብዱላዚዝ የርቀት ሙከራ እና በጋናዊው አጥቂ ናኑ ፖኩ የግንባር ኳስ በድጋሜ  ድቻዎችን ማስጨነቃቸውን ቀጥለዋል። ፖኩ ከ5 ደቂቃ ቆይታ በኃላም ከመሀመድ አላህ የደረሰውን ኳስ በግንባሩ የሞከረበት መንገድም ኢላማውን አይጠብቅ እንጂ በአስፈሪነቱ የሚነሳ ነበር። በእነዚህ የመጀመሪያ ደቂቃዎች የሚፈሉግትን ማሳካት ያልቻሉት ባለሜዳዎቹ ጥረታቸው በዛው አልቀጠለም። ድቻዎችም በሂደት ድፍረትን እያገኙ በጋራ ከመከላከል ባለፈ በጃኮ አራፋት መሪነት ወደ ዛማሌክ የሜዳ ክልል ለመግባት የሚሞክሩባቸው አጋጣሚዎች ቀስ በቀስ ይታዩ ነበር። በተለይ 10ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ በዛማሌክ ሳጥን አቅራቢያ የነጠቀውን ኳስ ለጃኮ ሲያሳልፍለት አጠረ እንጂ መልካም የሚባል አጋጣሚ ነበር። 32ኛው ደቂቃ ባሰም ሞርሲ ከሳጥን ውስጥ ያገኘውን ዕድል ሳይጠቀም ከመቅረቱ በቀር ዛማሌኮች ኳስን መስርተው ከሜዳቸው ሲወጡ ቢታዩም የኃይማኖት ወርቁ ፣ አብዱልሰመድ አሊ እና በዛብህ መለዮን የመሀል ሜዳ ጥምረት እንዳለፉ ኳሶቻቸው ወደ መስመሮች የሚላኩ ነበሩ። ወደቀኝ ባደለው ይህ እንቅስቃሴያቸውም የድቻ የግራ መስመርን በተደጋጋሚ መፈተናቸው አልቀረም። ሆኖም የድቻ የግራ መስመር ተከላካይ ተስፉ ኤልያስ እና ከጎኑ የነበረው የመሀል ተከላካይ ተክሉ ታፈሰ በተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲያከሽፉ ቆይተዋል። 44ኛው ደቂቃ ላይ ግን ኬንያዊው አልቢትር አወዛጋቢ ውሳኔ አሰልፈዋል። ዛማሌኮች በዛው መስመር በከፈቱት ጥቃት የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሀዚም ኢማም  ከሳጥን ወደ ውስጥ ለማሻገር የሞከረውን ኳስ ተስፉ ሸርተቴ ገብቶ በጀርባው ሲያድንበት አልቢትሩ በእጁ ነው የነካው በማለት የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም በመጠቀም አህመድ ማግቡሊ ዛማሌክን በድምር ውጤት አላፊ የምታደርግ ግብ አስቆጥሮ ቡድኖቹ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

እንደመጀመሪያው ሁሉ በሁለተኛው ግማሽ በሙሉ ሀይላቸው በማጥቃት የጀመሩት ዛማሌኮች ግብ ለማግኘት ሁለት ደቂቃ ብቻ ነበር ያስፈለጋቸው። የወላይታ ድቻ ተጨዋቾች ከወንድወሰን የተወረወረላቸውን ኳስ ለመቀባበል ሲሞክሩ በሰሩት ስህተት የተገኘውን ኳስ አህመድ ማግቡሊ ወደ ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት በግሩም ሁኔታ ከመረብ አገናኝቶታል። ሆኖም ጎሉ የጦና ንቦቹ ሀሳባቸውን ወደ ማጥቃቱ እንዲያደርጉ የገፋፋቸው ነበር። ከአራት ደቂቃዎች ቆይታ በኃላም ድቻዎች በዛማሌክ ግብ ግራ መስመር ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት ተስፉ ኤልያስ ሲያሻማ ሁለተኛው የግብ ቋሚ ላይ ይገኝ የነበረው ቁመተ መለሎው አማካይ አብዱልሰመድ አሊ በግንባሩ ማስቆጠር ችሏል። በድምር ውጤት ቡድኖቹን እኩል ካደረገችው ይህች ግብ መገኘት በኃላ 62 እና 63ኛው ደቂቃ ላይ በባሰም ሙርሲ የግንባር እና በኖኑ ፖኩ ኢላማውን የጠበቀ የረጅም ርቀት ሙከራዎች ሶስተኛ ግብ ለማግኘት ተቃርበው የነበሩት ዛማሌኮች ሜዳቸው ላይ የመጫወታቸውን ያህል ከፍተኛ ብልጫ መውሰድ አልቻሉም። 

ወላይታ ድቻዎችም ቢሆኑ ሙሉ ለሙሉ ወደ ጎላቸው ተስበው ከመከላከል ይልቅ የማጥቃት አጋጣሚዎች ሲከፈቱላቸው ወደ ፊት ለመሄድ ይሞክሩ ነበር። ሆኖም የመጫወቻ ሜዳው ጋር ካለመላመድ ጋር በተያያዘ መልኩ ይመስላል ቅብብሎቻቸውን መመጠን ሲቸገሩ ይታዩ ነበር። የአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ልጆች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በርካታ የግብ ዕድሎችን ፈጥረው የአቻነት ግብ አያግኙ እንጂ ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርባቸው እስከ 90ኛው ደቂቃ መዝለቅ አልተሳናቸውም። ዛማሌኮችም ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ ያገኟቸውን ዕድሎች ሁላ መጠቀም ሳይችሉ ወደ መለያያ ምት ለማምራት ተገደዋል።

በመለያ ምቱ ወቅት የወላይታ ድቻ መቺዎች ሆነው የተመረጡት ጃኮ አራፋት ፣ ተመስገን ዳባ ፣ አብዱልሰመድ አሊ እና ተክሉ ታፈሰ በሙሉ በተረጋጋ አኳኃን ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። ዛማሊኮችም የመጀመሪያ ሁለት ምቶቻቸውን በባሰም ሙርሲ እና አህመድ ሙጉቡሊ ወደ ግብነት ቢቀይሩም ቀጣዩ  የሀፍኒ ምት በግቡ አግዳሚ ሲመለስ መሀመድ አብዱላዚዝ የመታው የመጨረሻ ኳስ ደግሞ በወንድወሰን ገረመው ጥረት ድኗል። ወላይታ ድቻም የማይረሳውን ታሪክ በደመቁ በመፃፍ ዛማሌኮችን በሜዳቸው የሀዘን ማቅ አልብሷቸዋል። ድሉን ተከትሎም ድቻ ወደ ሁለተኛው ዙር የተሻሸጋገረ ሲሆን በመጪው ረቡዕ በካይሮ በሚደረገው የእጣ ማውጣት ስነስርዐት ወደ ምድብ ለመግባት የሚፋለመውን ተጋጣሚ የሚያውቅ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *