” በዚህ ቡድን ውስጥ አለመኖሬ ቁጭት ቢፈጥርብኝም በውጤቱ ኮርቻለሁ ” መሳይ ተፈሪ 

ወላይታ ድቻ ለመጀመርያ ጊዜ እየተሳተፈበት በሚገኘው የአፍሪካ መድረክ ብዙዎችን ባስገረመ መልኩ ከአፍሪካ ሃያላን አንዱ የሆነው ዛማሌክን ከውድድር በማስወጣት ወደ ሁለተኛው ዙር አልፏል።

በ2001 የተመሰረተው ወላይታ ድቻን ከምስረታው ጀምሮ ሲያሰለጥን የቆየውና ከወራት በፊት ከክለቡ ጋር የተለያየው መሳይ ተፈሪ ከትላንት ምሽቱ ጨዋታ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት በውጤቱ ደስታ እንደተሰማው ገልጿል። ” በጣም ደስ ብሎኛል። ውጤቱ የድቻ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ነው። ይሄ ውጤት የመጣው በቀላሉ አይደለም። የወላይታ ድቻን አነሳስ የሚያውቅ ሁሉ ይህ ውጤት ምን ማለት እንደሆነ ይረዳል። እዚህ ለመድረስ ብዙ የለፋ እና የልፋቱን እያገኘ የሚገኝ ክለብ ነው። ”

አሰልጣኝ መሳይ አምና ቡድኑ ወደ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚያሳልፈውን እድል የኢትዮጵያ ዋንጫን በማሸነፍ ቢያሳካም ቡድኑን በአፍሪካ ውድድር ከመምራቱ በፊት በመሰናበቱ የወላይታ ድቻ ታሪክ አካል መሆን አልቻለም። በዚህ ወቅት የቡድኑ አባል ባለመሆኑ የቁጭት ስሜት ተሰምቶት ይሆን? ይህን ሁኔታም እንዲህ ያስረዳል። ” ይህ ውጤት ሲመጣ በቡድኑ ውስጥ ባለመኖሬ የቁጭት ስሜት ቢሰማኝም በውጤቱ የተሰማኝ ኩራት ከፍተኛ ነው። ጨዋታውን በቴሌቪዥን እየተመለከትኩ በተለይ ደግሞ በመለያ ምቱ ወቅት በጭንቀት ስንቆራጠጥ እና ስፀልይ ነበር። በውጤቱ እውነተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ። በቀጣይም ከዚህ በላይ አንዲጓዙ ምኞቴ ነው። ” ያለው መሳይ በቀጣይ ጨዋታዎች ቡድኑ ማድረግ የሚገባውን በመግለፅ አስተያየቱን ቋጭቷል።

” በቀጣይ ቡድኑ ይህንን ስሜት ማስቀጠል ነው ያለበት። በዚህ ውጤት በፍፁም መዘናጋት የለባቸውም። ካሁን በኋላ ለሚኖሩ ጨዋታዎች በአእምሮ መዘጋጀት እና ካለፉ ስህተቶቻቸው ተምረው መቅረብ ከቻሉ ከዚህም በላይ መጓዘ እንደሚችሉ እተማመናለሁ። ” 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *