የወላይታ ድቻ ተጨዋቾች ስለድሉ ምን አሉ ?

“ትልቁ ጥንካሬያችን በህብረት መጫወታችን ነው” ወንድወሰን ገረመው

“ጎሉን በማስቆጠሬ ደስታዬ ወደር የለውም” አብዱልሰመድ አሊ

ትናንት ምሽት በቶታል ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ወላይታ ድቻ ዛማሌክን በመለያ ምት ሲረታ ከፍተኛውን ሚና ከተወጡ ተጨዋቾች መሀከል ወሳኟን ግብ ያስቆጠረው አብዱልሰመድ አሊ እና የመጨረሻዋን መለያ ምት ያዳነው ወንድወሰን ገረመው ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ወንድወሰን ገረመው

ውጤቱ የፈጠረበት ደስታ

እንደማንኛውም ዜጋ ታሪክ ስትሰራ የድሉ ባለቤትም ስትሆን ኩራት ይሰማሀል። በተለይ ደግሞ ከዚህ ቀደም ያልነበረን የመጀመርያ ታሪክ ስትሰራ የተለየ ስሜት ይፈጥርብሀል። እጅግ በጣም ነው ደስ ያለኝ። እንባ እየተናነቀኝ ነው የማወራህ። ውስጤ በጣም ሀሴት አድርጓል። ለዚህ ታሪክ በመብቃቴ ዕድለኛ ነኝ። ዛማሊክ እጅግ ጠንካራ ቡድን ነው። በጣም አቅም አላቸው። የመስመር ላይ ኳስ አጨዋወታቸው አደገኛ ነው። ይህን ጠንካራ ቡድን ተጋድለን በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ማጣርያ ዙር ማለፈችን ደግሞ ብቃትህን የምታረጋግጥበት ድል መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ።

ድሉ ለኢትዮዽያውያን ተጨዋቾች የሚያስተላልፈው መልክት

በጣም ትልቅ መልክት አለው። ኢትዮዽያውያን ተጨዋቾች አቅም እንዳላቸው እና ታሪክ መቀየር እንደሚችሉ ማሳያ ነው። ከየትኛውም አፍሪካ ሀገር አናንስም። ከተሰራበት አዕምሯችን ላይ የተሻለ ነገር ማድረግ እንችላለን። ውጤቱ የኢትዮዽያን እግርኳስ ዳግም ለማንሳት የሚያስችል የታሪክ አጋጣሚ ብዬ ነው የማስበው።

ስለቡድኑ ጥንካሬ

በቂ ዝግጅት አድርገናል። በሙሉ ራስ መተማመን ነው ወደዚህ የመጣነው። አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብን ተነጋግረናል። ትልቁ ጥንካሬያችን በህብረት መጫወታችን እና የግለሰብ ቡድን አለመሆናችን ነው። በስነ ልቦናው ረገድ የነበረን ጥንካሬም የድላችን ትልቁ ጥንካሬ ነው። ሌላው በሜዳቸው በደጋፊዎቻቸው ፊት የእነሱን ጫና በእራሱ በመቋቋም መውጣት ትልቅ ጥንካሬ ነው ብዬ አስባለው።

መለያ ምቶች የማዳን አቅም

በግብ ጠባቂነት ህይወቴ ውስጥ ብዙ መለያ ምት የማዳን ታሪኮች አሉኝ። በልምምድ ወቅት እንኳ ሳይቀር ብዙ አድን ነበር። መለያ ምት የመመለስ አቅሙ እንዳለኝ በሚገባ አውቃለው። መለያ ምት የማዳን ብቻ ሳይሆን የመመምታቱ አቅሙ አለኝ። ትናትም የቡድናችን አምስተኛ መቺ ነበርኩ። ሆኖም ቀድሞ ጨዋታው አለቀ። በጥሎ ማለፉ ላይም ታሪክ ሲሰራ ደስታዬን የገለፅኩት እኔ ነበርኩ ትናትም ሌላ ታሪክ ሲሰራ ደስታዬን በተመሳሳይ ሁኔታ የገለፅኩት እኔ መሆኑ የነገሩን መገጣጠም አስገራሚ ያደርገዋል።

ስለ ቀጣይ ጉዞ…

ይህ ስብስብ ታረክ ለመስራት የተዘጋጀ ስብስብ ነው። ገና ብዙ ታሪክም ይሰራል። በጣም አቅም ያላቸው እና የመታየት እድሉን ያላገኙ ተጨዋቾች ያሉበት ስብስብ ነው። በቀጣይ ሌላ ታሪክ የማይሰራበት ምንም ምክንያት የለም። ከዚህ በኋላ ብዙ ምዕራፎችን መጓዝ እንፈልጋለን። ጥሩ ስብስብ አለን። ሌላ ቀጣይ ታሪክ መስራት እንፈልጋለን።

አብዱሰመድ አሊ

ድሉ ፈጠረበት ስሜት

በመጀመርያ ክለቤ አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር በማለፉ በጣም ደስ ብሎኛል። በተለይ ደግሞ ጎል አስቆጥሬ በታሪክ ውስጥ ስሜን በማፃፌ ደስታዬን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል። ወደ ፊት ብዙ መስራት እንደምችል አቅም እንዳለኝ ያረጋገጥኩበት ጨዋታ ነው።

ለጨዋታው የነበራቸው ዝግጅት

ለዚህ የመልስ ጨዋታ በደንብ ተዘጋጅተናል። ጠንካራ ጎናችን እንዳለ ሆኖ በድክመታችን ላይ ብዙ ሰርተናል። እነሱንም ሀዋሳ ላይ ጥንካሬያቸውን አይተነዋል። መጠንቀቁ ላይ ትኩረት አድርገን በደካማ ጎናቸው ላይ አሰልጣኛችን ዘነበ ፍስሀ ሲያሰራን ነበር። የመስመር ላይ ኳሳችን እንደሚጫወቱ ተነግሮናል። በዚህ ላይም እነሱን ለማቆም ሰርተን ጥረታችንም ተሳክቶልን አሸንፈን ወጥተናል።

በድቻ እና ዛማሌክ መካከል ያለው ልዩነት…

በእግርኳሳዊ (ሜዳ ውስጥ ባለ) የዘጠና ደቂቃ እንቅስቃሴ ከሆነ በመካከላችን ምንም አይነት ልዩነት የለም። ኳስ ኳስ ነው። እኛም እነሱም እንችላለን። ሌሎችም ነገሮች እንዳሉ ቢሆንም ሜዳ ውስጥ ባለ ነገር ማለቴ ነው። እንዲያውም በእግርኳስ የግል ችሎታም ቢሆን እኛ የተሻልን ነን። በጣም በእኛ ሲገረሙ ነበር። ልዩነቱ የማመን እና የመቀበል ጉዳይ ነው። ብዙ ተብሎላቸው ሰቅለናቸው ነበር። ሜዳ ላይ የተመለከትነው ግን ይሄ አይደለም እንዲያውም በተሻለ የተንቀሳቀስነው እኛ ነበርን።

መለያ ምቱን ሲመታ የነበረው በራስ መተማመን

እንደማገባው እርግጠኛ ሆኜ ነው የሄድኩት። ከእኛ ይልቅ እነሱ ጫና ውስጥ እንደነበሩ አስባለው ። ግብ ጠባቂው ደግሞ ቁመት እንጂ ብዙ አቅም የሌለው በመሆኑ የመረበሽ ስሜት አልተሰማኝም ። እንዲያውም እየሳኩበት ነበር አየው የነበረው። ጎሉን በማስቆጠሬ ደስታዬ ወደር የለውም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *