ሮበርት ኦዶንካራ ከዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ውጪ ሆኗል

ዩጋንዳ ከሳኦቶሜ ፕሪንስፔ እና ማላዊ ጋር ላለባት የወዳጅነት ጨዋታ የተጠራው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ በጉዳት ምክንያት ከክሬንሶቹ ስብስብ ውጪ ሆኗል፡፡

ሮበርት ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ በኬሲሲኤ 1-0 ሽንፈት ሲገጥመው ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላም ጉዳት እንደገጠመው ተጠቁሟል፡፡ ከጉዳቱ በግዜው ማገገም ባለመቻሉ የዩጋንዳው አሰልጣኝ ሰባስቲያን ዴሳቤር የኬሲሲኤውን የግብ ዘብ ቻርለስ ሉዋጎን በሮበርት ምትክ ወደ ቡድናቸው አካተዋል፡፡ ሮበርት ፈረሰኞቹ በሀዋሳ ከተማ 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት በሊግ ጨዋታ ሲሸነፉ ለ64 ደቂቃዎች ተጫውቶ በጉዳት ከሜዳ ቢወጣም ክለቡ በነበረበት የቻምፒየንስ ሊግ ወሳኝ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል፡፡

ዩጋንዳ ካልተሳካ የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒየንሺፕ (ቻን) ዘመቻ በኃላ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ታደርጋለች፡፡ ሆኖም ሮበርት ከረጅም ግዜ በኃላ ወደ ቡድኑ የተመለሰ ቢሆንም በጉዳት ሳቢያ ጨዋታዎቹ ያመልጡታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *