ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ሽቅብ መውጣቱን ቀጥሏል

አዲስ አበባ ስታድየም በዕለቱ በሁለተኛነት ያስተናገደው የመከላከያ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በእያሱ ታምሩ እና ሳሙኤል ሳኑሚ ጎሎች ቡናን ባለድል በማድረግ ተጠናቋል።

መከላከያ ከሶዶ አንድ ነጥብ ይዞ ከተመለሰው ስብስቡ ምንም የመጀመሪያ አሰላለፍ ለውጥ ያላደረገ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ካሸነፈበት ጨዋታ ኤፍሬም ወንደሰንን እና ኤልያስ ማሞን ተጠባባቂ አድርጎ ለቶማስ ስምረቱ እና ክሪዚስቶም ንታንቢ የመሰለፍ ዕድል በመስጠት ነበር ጨዋታውን የጀመረው።

በፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸው አማካይነት የጦሩ ተጨዋቾች ኳስ ይዘው ከሜዳቸው እንዳይወጡ ጫና በመፍጠር የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ጨዋታውን ያሸነፉባቸውን ጎሎች ያገኙት የመጀመሪያው 45 ከመጋመሱ በፊት ነበር። ገና በ6ኛው ደቂቃ በግራ መስመር ተነጥሎ ኳስ የተቀበለው ታዳጊው የመስመር ተከላካይ ኃይሉ ገብረትንሳይ ወደ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ታፈሰ ሰረካን ካለፈ በኃላ ወደ ግብ የላካትን ኳስ እያሱ ታምሩ ሁለተኛው ቋሚ ጋር በመገኘት ማስቆጠር ችሏል። 17ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ መሀል ሜዳ አካባቢ የተቀማች ኳስ የደረሰችው ሳሙኤል ሳኑሚ ሁለት የመከላከያ ተጨዋቾችን አልፎ ወደ መከላከያ ሳጥን በመቅረብ በአቤል ማሞ መረብ ላይ ሁለተኛዋን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከዚህ በኃላ በነበረው እንቅስቃሴ ቡናዎች እንደወትሮው ለረጅም ሰዐት ኳስ ተቆጣጥረው በተቃራኒ የሜዳ ክልል ከመማሳለፍ ይልቅ ወደ ራሳቸው አጋማሽ ቀረት ብለው በተመሳሳይ በአምስት አማካዮች የተዋቀረው የመከላከያ የአማካይ ክፍል ወደ ግብ ክልላቸው እንዳይጠጋ ማድረግ ላይ አተኩረዋል። በማጥቃቱ በኩል ያለቀላቸው የሚባሉ ዕድሎችን መፍጠር ባይችሉም ከሚነጥቋቸው ኮሶች ሳሙኤል ሳኑሚን መዳረሻ በማድረግ ድንገተኛ ጥቃት ሲሰነዝሩ ከመከላከያዎች የተሻለ አስፈሪነት ነበራቸው።

የመከላከያዎች የመጀመሪያ አጋማሽ የማጥቃት ሂደት ለኢትዮጽያ ቡና መከላከል እጅግ የተመቸ ነበር። የቡድኑ የዘወትር ችግር የሆነው ወደ መሀል የጠበበ የማጥቃት ሂደት ከተጋጣሚ ተጨዋቾች ቦታ አያያዝ ጋር ተዳምሮ ቅብብሎችን እንደልብ ለማድረግ ያላስቻለ ነበር። ይህ በመሆኑ ቡድኑ ኳስ ይዞ ለመጫወት ቢሞክርም የማግባት ዕድል መፍጠር ብቻ ሳይሆን ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክልል መግባት ራሱ እንዲከብደው አድርጎታል። ከአምስቱ የጦሩ አማካዮች ውስጥ የኢትዮጵያ ቡናን የመስመር ተከላካይ ኃይሉ ገብረየስን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ሊያውም በመከላከል ሂደት ላይ ብቻ ወደ ጎን አስፍቶ ሲቆም ይታይ የነበረው ሳሙኤል ሳሊሶ ብቻ ነበር። በመሆኑም ቡድኑ ያደረግቸው ሙከራዎች ምንይሉ ወንድሙ ከሳጥን ውስጥ ቴውድሮስ ታፈሰ ደግሞ ከሳጥን ውጪ ወደ ጎል መተዋቸው ኢላማቸው ያልጠበቁ ሁለት መከራዎች ብቻ ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ማራኪ ወርቁን በአማኑኤል ተሾመ ቀይረው በማስገባት የቡድናቸውን አሰላለፍ ወደ 4-4-2 ዳይመንድ ቀይረዋል። ቅያሪውን እና የቡድኑ የመስመር ተከላካዮች ከመጀመሪያው በተሻለ ወደ ፊት ጠጋ ብሎ ለመጫወት መሞከር መከላከያን ወደ ተሻለ የማጥቃት ስርዐት አምጥቶታል። ያም ቢሆን ግን የኢትዮጵያ ቡናን ጥንቃቄ ላይ ያተኮረ አደረጃጀት ማለፍ ለጦሩ ተጨዋቾች ቀላል አልሆነም። በሙከራ ደረጃም 66ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ከተከላካዮች ቀምቶ የሰጠውን ኳስ ማራኪ ከሳጥን ውጥ ሞክሮ ሀሪሰን በቀላሉ እስኪይዝበት ደረስ ቡድኑ ከቅጣት ምት ብቻ የተገኙ ዕሎችን ነው የፈጠረው። እነርሱም የመጀመሪያው በዳዊት እስጢፋኖስ ተመቶ ወደውጪ ሲወጣ የምንይሉ ወንድሙ ሌላኛው ቅጣት ምት ደግሞ በሀሪሰን ሄሱ ድንቅ ብቃት መክኗል።

በመጀመሪያው አጋማሽ አቀራረባቸው የቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው አማካይ አማኑኤል ዮሀንስ መሪነት መከላከያዎች ከዳዊት እስጢፋኖስ እንቅስቃሴ እድሎችን እንዳያገኙ ተጨዋቹን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል። በማጥቃቱ በኩልም የመከላከያዎች የኃላ ክፍል ወደ መሀል ሜዳው በሚጠጋበት ወቅት የሚከፍቷቸው ጥቃቶች በቁጥር ባይበራከቱም አደግኝነታቸው ግን የጎላ ነበር። በተለይ 63ኛው ደቂቃ ላይ አስራት ቱንጆ በቀኝ መስመር በኩል ይዞት ወደ ውጥ የገባው ኳስ የሚጠቀስ ነበር። 66ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ከግራ መስመር ካሻማው ኳስ ክሪዚስቶም ንታንቢ በግንባሩ የሞከረበት አጋጣሚ የቡናን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ ለማድረግ ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም በአቤል ማሞ ጥረት ሊድን ችሏል።

በዚህ መልኩ በጥሩ ፉክክር የቀጠለው ጨዋታ ከ70ኛው ደቂቃ በኃላ የተጨዋቾች ጉሽሚያ ሲበራከትበት ታይቷል። ዳዊት እስጢፋኖስ ከቡና አማካዮች ጋር በሚገንኝባቸው አጋጣሚዎች ይፈጠሩ የነበሩ ሰጣ ገባዎች በሎሎች ላይም ቀጥለው ሽመልስ ተገኝ እና አስናቀ ሞገስን በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲሰናበቱ ምክንያት እስከመሆን ደርሰዋል። ፌደራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘውም በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ከሁለቱ ቀይ ካርዶች ሌላ አራት የቢጫ ካርዶችን ለመምዘዝ ተገደዋል። 79ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ በመልሶ ማጥቃት ከፈጠረው ጥሩ አጋጣሚ ውጪም በጨዋውታ ጠንካራ ሙከራዎች አልታዩም። ኢትዮጵያ ቡናዎች ኤልያስ ማሞን ቀይረው በማስገባት ጨዋታውን አቀዝቅዘው ወደ ራሳቸው ቁጥጥር በማምጣት መሪኑታቸውን አስጠብቀው በአሸናፊነት አገባደዋል። በውጤቱም በሁለተኛው ዙር ሶስቱንም ጨዋታዎች ያሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና ከጅማ አባ ጅፋር ጋር በነጥብ እና በግብ ልዩነት ዕኩል በመሆን ብዙ ባገባ በሚለው ህግ መሰረት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *