ሪፖርት | ፋሲል ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር አቻ ተለያይተዋል

ጎንደር አፄ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ የተገናኙት ሁለቱ ክለቦች ጨዋታቸውን ያለግብ አጠናቀዋል። ሀዋሳ ላይ ሽንፈት የገጠመው መሪው ደደቢትን መቅረብ የሚችሉበትን ዕድልም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

በ17ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ከተጠቀሙት ስብስብ በርካታ ለውጥ ያደረጉት ፋሲል ከተማዎች ነበሩ። አዲስ አበባ ላይ 3-1 በተረታው የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሰይድ ሁሴን በቅጣት አብዱርሀማን ሙባረክ ደግሞ በቅጣት ሳቢያ በፍፁም ከበደ እና ኤርሚያስ ኃይሉ ተተክተዋል። ከዚህ በተጨማሪም አማካይ ክፍል ላይ ኤፍሬም አለሙ ሔኖክ ገምቴሳን እንዲሁም ከፊት ደግሞ ሀሚስ ኪዛ ራምኬል ሎክን ለውጠዋል። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ግን ድሬደዋን ካሸነፈው ስብስብ የልነበረው አጥቂ መስመር ላይ ጉዳት የገጠመው ተመስገን ገብረኪዳን ሲሆን ቦታው በሳምሶን ቆልቻ ተሸፍኗል።

ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ የፋሲል ከተማ ክለብ እና ደጋፊዎች ማህበር ለጅማ አባ ጅፋር በፋሲል ግንብ መልክ የተቀረፀ ምስል በሸልማት መልክ አበርክተዋል። ስጦታውንም የጅማ አባ ጅፋር ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ናስር አ/ዲጋ ተቀብለዋል ፡፡

በመጀመሪያው 15 ደቂቃ ፋሲል ከተማ የተሻለ እቅስቃሴ ማሰየት የቻለ ሲሆን 12ኛ ደቂቃ ላይ ኤፋሬም አለሙ ካደረገው ሙከራ አራት ደቂቃዎች በኃላ ሀሚስ ኪዛ ከአምሳሉ ጥላሁን የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ግብ አስቆጠጠ ሲባል ያመከነው አጋጣሚ ለቡድኑ የሚያስቆጭ ነበር። በጅማ አባ ጅፋር በኩል በ14ኛው ደቂቃ ኄኖክ ኢሳያስ ያደረገው ሙከራ የሚጠቀስ ሲሆን በፋሲሎች በኩል ደግሞ 23ኛው ደቂቃ ላይ ከኤፍሬም አለሙ የተሻገረውን ኳስ ሀሚዝ ኪዛ በድጋሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጅማ አባጅፋሮች 29ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙት የማዕዘን ምት ሲሻማ  ሳምሶን ቶልቻ በግንባሩ በመግጨት የሞከረው ሌላው የእንግዳው ቡድን የመጀመሪያ አጋማሽ ሙከራ ነበር። ከረጅም ጊዜ በኃላ ከጉዳት ተመልሶ በሁለተኛው ዙር ክለቡን ሲያገለግል የቆየው ያሬድ ባየህ 38ኛው ደቃቂ ተጎድቶ በመውጣቱ ከድር ኸይረዲን ተክቶት ወደ ሜዳ ገብቷል።  ከበድ ባለ ንፋስ የቀላቀለ ዝናብ ታጅቦ በቀጠለው ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋሮች የተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም መሀል ሜዳ ላይ ያገኙት የበላይነት የፋሲል ከተማን የተከላካይ መስመር በተደጋጋሚ አልፎ ለመግባት በቂ አልነበረም። የአጋማሹ የመጨረሻው የግብ ዕድል የተፈጠረውም በባለሜዳዎቹ በኩል ሲሆን 44ኛው ደቂቃ ላይ ሀሚስ ኪዛ ላይ ጥፋት ተሠርቶ የተገኘው የቅጣት ምት አምሳሉ ጥላሁን ቢያሻማም የፋሲል ተጨዋቾች ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በዚህም መልኩ ቡድኖቹ ያለግብ ወደ እረፍት አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ንፋስ የቀላቀለው ዝናብ ተጠናክሮ መቀጠሉ የአየር ሁኔታውን ይበልጥ አክብዶታል። ሆኖም የንፋሱ አቅጣጫ ወደ ጅማ አባ ጅፋር የሜዳ ክልል ይሄድ የነበረ በመሆኑ ባለሜዳዎቹ ፋሲሎች ተጭነው የመጫወት ዕድል ገጥሟቸዋል። 69ኛው ደቃቂ ላይ ሚኬል ሳማኬ ተጎድቶ ጨዋታው ለተወሰነ ደቂቃ ተቆርጦ የነበረ ሲሆን በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ለመመልከት ባንችልም በ68 እና 71ኛው ደቂቃዎች ላይ ሀሚስ ኪዛን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ራምኬል ሎክ ያደረጋቸው መከራዎች የተሻሉ ነበሩ። ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት ሲጠናቀቅ የፋሲል ከተማው ግብ ጠባቂ ሚኬል ሳማኬ በድጋሜ ጉዳት አስተናግዷል። ፋሲል ከተማ በቀጣይ ለሚጠብቀው የአማራ ደርቢ የሁለቱ ተጨዋቾች ጉዳት ነገሮችን ሊያከብደበት እንደሚችልም ይታሰባል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ጅማ አባ ጅፋር

ጨዋታው እንደ አጠቃላይ  ጥሩ ነው። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ መጫወት ችለናል። በሁለተኛው  አጋማሽ ግን የአየር ሁኔታው ዝናብ ነፋስ የቀላቀለ ስለ ነበር ተቸግረናል።  እናም የምንፈልገውን አይነት ጨዋታ መጫወት አልቻልንም። ነገርግን ያለውን ሁኔታ ተቋቁመን  ነጥብ ይዘን መውጣት ችለናል። እዚህ ስንመጣ አሸንፈን ለመሄድ ነው የመጣነው። ካልተቻለ ደግሞ  አቻ ለመውጣት። ምክንያቱም ፋሲል  አጠገባችን ነው እኛን ካሸነፈ ይደርስብን ነበር። እንዳያሸንፈን ጥንቃቄ አድርገን ነበር ስንጫወት ነበር።

አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ – ፋሲል ከተማ
ጨዋታው በሁለተኛው ዙር ካደረግናቸው  ጨዋታዎች ሁሉ የተሻለ ነው። በጣም ተጭነን የተሻለ የጎል ዕድል ለመፍጠር ሞክረናል። በአጨዋወት በኩልም እኛ የተሻልን ነበርን። ቢሆንም ግን ያገኝናቸውን  የጎል እድሎች መጠቀም አልቻልንም  እሱን እንደችግር  አይተናል ። ከአሁን በፊት ቡድኑን እናውቀዋለን። ረጃጅም ኳሶች ነው የሚጠቀመው። እናም በመስመር  የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ 75 % ማጨናገፍ ችለናል። አዲስ ከመጡ ተጨዋቾች መሀከል ሰንደይ ሙቱኩ የተሻለ  እንቅስቃሴ አድርጓል። ይሄን ነገር በዚህ  ከቀጠለ ጥሩ ነው። በግልም ሆነ በጋራ ያሳየው ነገር ጥሩ ነው  ለቀጣይ  12 ጨዋታዎች አሉ በነሱ የተሻለ ነገር እንሰራለን።


በኢንተርኔት መቆራረጥ ምክንያት ሪፖርቱን በወቅቱ ማቅረብ አልቻልንም።


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *