የጃኮ አራፋት እና በዛብህ መለዮ ፈላጊ ክለቦች ታውቀዋል

በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ወላይታ ድቻ ከግብፁ ዛማሌክ ባደረገው የደርሶ መልስ እንቅስቃሴ በግብፅ ክለቦች አይን ውስጥ የገቡት ጃኮ አራፋት እና በዛብህ መለዮ በሰኔ ወር መጨረሻ የሚያቀኑበት ክለብ ታውቋል፡፡

አምና ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሀዋሳ ከተማን ተቀላቅሎ በመጀመሪያው አመት ስኬታማ የነበረው ቶጎዊው አጥቂ ጃኮ አራፋት በክረምቱ ወደ ወላይታ ድቻ አምርቶ ክለቡ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የአፍሪካ ወድድር ላይ ወሳኝ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተከትሎ በሰኔ ወር መጨረሻ የግብፁ ክለብ ኤል ኤታንግ ኤል ሀርቢን ለመቀላቀል ከስምምነት መድረሱ ታውቋል፡፡ ተጫዋቹ ከኤል ሀርቢ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ኡመድ ኡኩሪ ከሚጫወትበት ስሞሀ ጋርም ስሙ የተያያዘ ሲሆን የኤል ሀርቢ ዝውውር እክል ከገጠመው ወደ ስሞሀ ሊያመራ ይችላል።

በዛብህ መለዮ ሌላው በክረምቱ ወደ ግብፅ የሚያመራ ተጫዋች ነው። የበዛብህ ከጃኮ የሚለየው ግን የሙከራ ጊዜ ለማሳለፍ መጓዙ ነው። ተጫዋቹ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፀው ከሆነ በኤል ኤንታግ ኤል ሀርቢ የሁለት ወራት ሙከራን የተሰጠው ሲሆን በሙከራው አመርቂ እንቅስቃሴን ካሳየ ወደ ክለቡ እንደሚቀላቅሉት ጉዳዩን የያዘለት ወኪል እንደገለፀለት ተናግሯል።

ኤል  ኤንታግ ኤል ሀርቢ በ2016/17 የውድድር አመት ኢትዮጵያዊው አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ የተጫወተበት ክለብ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *