ጋና 2018 | ሉሲዎቹ ነገ ሊብያን ያስተናግዳሉ

በ2018 ጋና ለምታስተናግደው የቶታል አፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የመጀመርያው ዙር የማጣርያ ጨዋታውን ወደ ካይሮ በማቅናት ሉሲዎቹ የሊቢያ አቻቸውን 8-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በመርታት ጨዋታ አቅልለው ተመልሰዋል። ነገ 10:00 ላይም በአአ ስታድየም ላይ የመልስ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ከካይሮ ከተመለሱበት ጊዜ አንስቶ ከቡድኑ ጋር አብረው ካልተጓዙት 7 ተጫዋቾች መካከል 5 ተጫዋቾች ዳግም ከቡድኑ ጋር በመቀላለቀል የዝግጅቱ አካል ሆነው የቀጠሉ ቢሆንም  ግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ እና አማካይዋ ብርቱካን ገ/ክርስቶስ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለው እንዲሰሩ ጥሪ ቢቀርብላቸውም አለመምጣታቸው አስገራሚ ሆኗል።  በልምምድ ወቅት ባጋጠማት መጠነኛ ጉዳት የተነሳ ተከላካይዋ ገነሜ ወርቁ ለነገው ጨዋታ የመድረሷ ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን የተቀሩት የቡድኑ ተጨዋቾች ለነገው የመልስ ጨዋታ በሙሉ ጤንነት ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸውን ለማቅ ችለናል።

የሊቢያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ትላንት እኩለ ሌሊት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ዛሬ 10:00 በሚጫወቱበት አዲስ አበባ ስቴዲየም የመጨረሻ ልምምድ ሰርተዋል።

አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ለጨዋታው የተለየ ግምት እንደምትሰጥ እና በነገው ጨዋታ ላይ ብዙ ለውጥ እንደማይኖር ገልፃ ከውጤት ባሻገር የቡድኑ ቀጣይነት ላይ ለመስራት በማሰብ በመጀመርያው ጨዋታ ላይ የተጠቀመችባቸውን 11 ተጫዋቾች አብዛኛውን እንደምትጠቀምባቸው ለሶከር ኢትዮዽያ ገልፃለች ።

ነገ በ10:00 ላይ የሚካሄደውን የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ሩዋንዳውያን ዳኞች የሚመሩት ይሆናል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *