ሪፖርት | ፋሲል ከተማ ደደቢትን አሸንፎ ከመሪነት አውርዶታል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዛሬ በጎንደሩ ፋሲለደስ ስታዲየም በተስተናገደ ጨዋታ ፋሲል ከተማ ደደቢትን በፊሊፕ ዳውዝ ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል።

በዛሬው ጨዋታ ይስሃቅ መኩሪያን በጉዳት፣ አምሳሉ ጥላሁንን ደግሞ በ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት ምክንያት ማሰለፍ ያልቻለው ፋሲል ከተማ ተጫዋቾቹን በሄኖክ ገምቴሳ እና ፍፁም ከበደ ተክቶ ወደሜዳ ገብቷል። ደደቢት ደግሞ በአቤል እንዳለ ምትክ ሰለሞን ሐብቴን በመጠቀም ጨዋታውን መጀመር ችሏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ አጥቅተው መጫወት የቻሉት ባለሜዳዎቹ ፋሲሎች ገና በአንደኛው ደቂቃ ወደ ግብ መድረስ ቢችሉም ኤርሚያስ ሀይሉ ያገኘውን ጥሩ የግብ አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት አፄዎቹ በ5ኛው ደቂቃ በኤፍሬም አለሙ፤ እንዲሁም በ17ኛው ደቂቃ በፊሊፕ ዳውዝ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በደደቢቶች በኩል በሰለሞን ሃብቴ፣ ሽመክት ጉግሳ እና ጌታነህ ከበደ የተደረጉ ሙከራዎች ዒላማቸውን ያልጠበቁ ነበሩ።

በጨዋታው 40ኛ ደቂቃ ፊሊፕ ዳውዝ ከኤፍሬም አለሙ የተሻገረለትን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በግሩም ሁኔታ በመጨረስ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። በ44ኛው ደቂቃ ፊሊፕ ዳውዝ ኤርሚያስ ሀይሉ ያሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ግብ ካስቆጠረበት ጋር ተመሳሳይ የሆነ አጋጣሚ ቢያገኝም በድጋሚ ኳስን ከመረብ ማሳረፍ አልቻለም። በጨዋታ አጋማሹ መጠናቀቂያም የደደቢቱ ሽመክት ጉግሳ ያገኘውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በዚህ ሁኔታ የመጀመሪያውን የጨዋታ ክፍለጊዜ በፋሲል ከተማ 1-0 መሪነት ተጠናቅቆ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች አፄዎቹ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን በ51ኛው ደቂቃ ላይም ሀሚዝ ኪዛ ከኤፍሬም አለሙ የተሻገረለትን ኳስ እጅግ በሚያስቆጭ መልኩ አምክኖታል፤ ከደቂቃዎች በኋላም በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ባሳየው ፍሊፕ ዳውዝ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። በቀሪ ደቂቃዎች ደደቢቶች አቻ የምታደርጋቸውን ግብ ለማግኘት የመሃል ሜዳ የበላይነቱን በመውሰድ አጥቅተው ቢጫወቱም በ73ኛው እና በ75ኛው ደቂቃዎች ጌታነህ ከበደ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጭ ከሞከራቸው እና በ78ኛው ኤፍሬም አሻሞ በተመሳሳይ ከርቀት ከመታው ኳስ ውጪ የፋሲል ከተማን የተከላካይ መስመር ሰብሮ መግባት ሲሳናቸው ተስተውሏል። ፋሲል ከተማዎችም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ውጤታቸውን ለማስጠበቅ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ 1-0 በሆነ ውጤት ጨዋታው አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

በጨዋታው ውጤት መሠረት አፄዎቹ ከነበሩበት 6ኛ ደረጃ ሁለት ደረጃዎችን ከፍ በማለት በ4ኛ ደረጃ ሲቀመጡ ለረጅም ሳምንታት የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ተቀምጦ የቆየው ደደቢት የጅማ አባ ጅፋርን ማሸነፍ ተከትሎ ወደ 2ኛ ደረጃ ለመውረድ ተገዷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

መሳይ ተፈሪ – ፋሲል ከተማ

ጨዋታው ጠንካራ ጨዋታ ነበር። ደደቢት ለዋንጫ እየተፎካከረ ያለ ቡድን ነው፤ እኛም ወደዛ ሪትም ለመግባት እየሞከርን ነበር። እነሱ ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም ተሳክቶልን ውጤት ይዘን ለመውጣት ችለናል፡፡ በሁለት ጨዋታዎች 3 ጎሎችን ማስቆጠር ችለናል፤ ስንከላከልም ያለውን ውጤት ለማስጠበቅ ጥሩ እያደረግን ነው፡፡

ጌቱ ተሾመ – ደደቢት

ዛሬ ጨዋታው ጥሩ ነበር። 90 ደቂቃ አጥቅተን ተጫውተናል፤ ግን ተሸንፈን ወጥተናል። ምንም ማድረግ አይቻልም። ወደ ጎንደር የመጣነው 3 ነጥብ ይዘን ለመሄድ ቢሆንም አልተሳካም፡፡ የደጋፍው ድባብ አሪፍ ነበር። ዳኛው ግን አልፎ አልፎ ይጫነን ነበር።