ኮንፌድሬሽን ዋንጫ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከውድድር ውጪ ሆኗል

በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ምድብ ለመግባት ብራዛቪል ላይ ካራን የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሆኗል፡፡ ፈረሰኞቹ በካራ በመለያ ምቶች 5-3 ተሸንፈው ነው ወደ ምድብ ሳያልፉ የቀሩት፡፡

በመጀመሪያው ጨዋታ 1-0 ያሸነፉት ጊዮርጊሶች በጨዋታው በተጋጣሚያቸው የጨዋታ ብልጫ ተወስዶባቸዋል፡፡ ካራዎች በ34ኛው ደቂቃ ንጎማ ምቦ በ34ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ መደበኛውን የጨዋታ ክፍለጊዜ 1-0 አሸንፈዋል፡፡ በአጠቃላይ ውጤት 1-1 በመሆናቸውም አላፊውን ለመለየት በተሰጡት የመለያ ምቶች ባለሜዳዎቹ ካራዎች 5-3 አሸንፈው ወደ ምድብ ማምራታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከተመቱት መለያ ምቶች መካከል የበኃይሉ አሰፋ እና ምንተስኖት አዳነ ኳሶች የመከኑ ነበሩ።

ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ወላይታ ድቻ በያንግ አፍሪካንስ ተሸንፎ ከውድድር መሰናበቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ክለቦች የዘንድሮው ዓመት የአፍሪካ ክለቦች ውድድር ጉዞ እዚህ ላይ አብቅቷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ አምና የዶሊሴውን ክለብ ሊዮፓርድስን ቢረቱም በኮንጎ መዲና ክለቦችን ግን ከውድድር ማስወጣት አልቻሉም፡፡ እ.ኤ.አ. 2005 በኤትዋል ዱ ኮንጎ ሲሸነፉ በ2018 በካራ ተረተው ከውድድር ወጥተዋል፡፡

ፈረሰኞቹ አምና በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ምድብ ድልድል ውስጥ መካተት ያቸሉ ቢሆንም በዘንድሮው የውድድር ዓመት ደካማ የአፍሪካ የክለቦች ውድድር ጉዞን አድርገዋል፡፡