ሪፖርት | የወላይታ ድቻ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጉዞ በያንጋ ተገትቷል

ወላይታ ድቻ በመጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታው ዛሬ በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም ያንግ አፍሪካንስን ገጥሞ በጃኮ አራፋት ብቸኛ ጎል ቢያሸንፍም ዳሬሰላም ላይ በተቆጠሩበት ሁለት ግቦች ምክንያት 2-1 በሆነ ድምር ውጤት ከውድድሩ ውጭ ሆኗል፡፡

ጨዋታው በዩጋንዳዊው ዳኛ ቺላንጌት አሊ ከተያዘለት ሰአት ቀድም ብሎ 9፡54 ላይ ነበር የጀመረው። የመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ለወላይታ ድቻ እጅግ ወሳኝ የነበሩ እና በርካታ የግብ አጋጣሚዎች እየተፈጠሩባቸው ነበሩ። የጦና ንቦቹ ገና በጊዜ ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመግባት ያደረጉት እንቅስቃሴም እልህ አስጨራሽ ነበር። 2ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘችውን የማዕዘን ምት ያሬድ ዳዊት መሬት ለመሬት ሲያሻግራት በርካታ ተጫዋቾችን አልፋ ጃኮ አራፋት እግር ስር ስትገባ ቶጎዊው አጥቂ ወደ ግብነት በመለወጥ ድቻዎችን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ በጨዋታው በተለይ የፊት መስመር አጥቂው ጃኮ ከሌሎቹ ተጨዋቾች የተሻለ ዕድሎችን ያገኘ ቢሆንም በተደጋጋሚ ወደ ግብነት መለወጥ ሲሳነው ተመልክተናል፡፡ በተለይ ከ15ኛው ደቂቃ በኃላ ወላይታ ድቻዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እንደ አማራጭ የወሰዷቸው በረጅሙ የሚጣሉ ኳሶች በግብ ጠባቂው ሮስታንድ ጄሁ በቀላሉ ሲያዙ አስተውለናል።

ያንጋዎች በመስመር በሚመጡ ኳሶች ከወላይታ ድቻ የተሻለ የኮሪደር ብልጫ ነበራቸው። በተለይ ዚምባብዌያዊው የመስመር ተጫዋች ኦቤሪ ቺሩዋ የሚያደርገው ፈጣን እንቅስቃሴ የወላይታ ድቻን የተከላካይ ስፍራ ሲያስጨንቅ ታይቷል። 16ኛው ደቂቃ ላይ ማዊኒ አሊ ከመስመር እየገፋ ገብቶ ለፕላስ ቡስዊታ ሰጥቶት አጥቂው አክርሮ ቢመታትም ተክሉ ታፈሰ እንደምንም ተንሸራቶ አውጥቶበታል ፡፡ ወላይታ ድቻወች እንደነበራቸው የማጥቃት ሀይል ያገኙትን የግብ እድሎች ወደ ግብነት መለወጥ ላይ እና ወደ ያንግ አፍሪካንስ የግብ ክልል ሲደርሱ የሚታዩት የሚቆራረጡ ኳሶች መብዛታቸው ደካማ ጎኖቻቸው ነበሩ። 19ኛው ደቂቃ ላይ በሌላኛው የግብ አጋጣሚ የያንጋ አፍሪካ ግብ ጠባቂ ሮስታንድ ጄሁ ኳስ ለማራቅ ግቡን ለቆ በወጣበት ሰአት ወደ እጅ ውርወራ የወጣችዋን ኳስ ዘላለም ኢሳያስ ወርውሯት የግብ ጠቢቂውን መውጣት የተመለከተው እዮብ አለማየሁ በቀጥታ ቢመታም ሙከራው አግዳሚውን ታኮ የወጣ ነበር።

ያንጋዎች በተለየ መልኩ ለማጥቃት ሲጠቀሙበት የነበረው የመስመር  አጥቂው  ኦቤሪ ቺሩዋ ጥሩ ጨዋታን አሳልፏል። ለዚህም መሳያ የሚሆነው 25ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት አክርሮ የመታት ኳስ እንደምንም በተከላካዮች ተጨርፋ ወደ ውጪ መውጣቷ ነው። በድጋሚ ኦቤሪ ከአንድ ደቂቃ በኃላ ወደ ግብ በቀጥታ መሬት ለመሬት የመታትን ኳስ ተስፉ ኤልያስ እንደምንም አውጥቶበታል ፡፡ የወላይታ ድቻ የተከላካይ ክፍል ኳስን መስርቶ ከመጫወት ይልቅ በረጃጅሙ እየጣሉ በጃኮ አራፋት ለመጠቀም ቢያስብም እምብዛም ስኬታማ አልሆነም። 29ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ አለማየሁ ካሻገረውን ኳስ በዛብህ መለዮ ለጃኮ አመቻችቶለት ጃኮ ከእግሩ ላይ ኳሷ አምልጣዋለች። ያንጋ አፍሪካንሶችም ከድቻ ባልተናነሰ መልኩ በርካታ ጊዜ የሚያስቆጩ ዕድሎችን ቢፈጥሩም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚህ በኩል 39ኛው ደቂቃ ላይ ኦቤሪ ፓፒ ከወንደሰን ገረመው ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያንጋን አቻ የምታደርግ አጋጣሚ ማምከኑ የሚጠቀስ ነው። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል የሱፍ ሚሄሎ በአግባቡ የላከለትን ኳስ አብደላ ሻሂቡ በግንባሩ የገጨበት አጋጣሚም በድቻዎች ላይ ተጨማሪ ጫና ልትፈጥር የተቃረበች ሙከራ ነበረች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተለይ የመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች በፍፁም የማጥቃት ሀይል የተጫወቱበት ነበር። ያንጋዎች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት እንዲሁም አራት የነበሩትን የኃላ ስፍራ ተጨዋቾች ወደ አምስት ከፍ በማድረግ ተከላክለው የወጡበት ነበር። ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ የሱፍ ሚሂሉ ከርቀት የመታት ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት ቅፅበት አስደንጋጭ ሙከራ ነበር። ወላይታ ድቻዎች በእንቅስቃሴ የተሻሉ ቢመስሉም ያንጋዎች ግን በርካታ ሙከራዎች ማድረጋቸው አልቀረም። በተለይ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ኦቤሪ ቺሩዋ መስመር ላይ በግሉ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እጅግ አሰገራሚ ነበር። ለዚህም መሳያ የሚሆነው በድቻ ተከላካዮች ጥረት አልተሳካለትም እንጂ በሁለት አጋጣሚወች ያለቀላቸውን ዕድሎች ማግኘቱ ነው። 60ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳዊት ከበዛብህ መለዮ የተቀበለውን ኳስ ይዞ ከግቡ ትይዩ በሆነ ቦታ ላይ ቢገኝም ማስቆጠር አልቻለም። ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ በተመሳሳይ ቦታ በመልሶ ማጥቃት ወደ  ድቻ የግብ ክልል የደረሱት ያንጋዎች ሀሰን ካሚሶ ያሻገረለትን ኳስ የሱፍ ሚሂሉ ወደ ግብ ቢመታም ወጥቶበታል።

ወላይታ ድቻዎች ተጭነው የተጫወቱበት እና ያንጋወች በጥብቅ መከላከልን የመረጡባቸው የመጨረሻዎቹ  10 ደቂቃዎች ለወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ጭንቀት የፈጠሩ ነበሩ። የሚያስቆጩ  አጋጣሚዎች ተገኝተው በቀላሉ የመከኑበት ጊዜም ነበር። 90ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ በሚገባ የሰጠውን ኳስ በዛብህ መለዮ ማንም አጠገቡ በሌለበት ሰአት ግልፅ ዕድል ቢያገኝም ሙከራው ወደ ላይ የተነሳ ነበር። ድቻዎች በጭማሪው ሰአት በቸርነት ጉግሳ አማካኝነት ሌላ አጋጣሚ ቢያገኙም ማስቆጠር ሳይችሉ በጨዋታው 1-0 ብቻ አሸንፈው በድምሩ 2-1 ተረተው ወደ ምድብ ድልድሉ ሳይገቡ ቀርተዋል።