ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደደቢት ከ መቐለ ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ዛሬ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ደደቢት መቐለ ከተማን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጀመራል። በጨዋታው ላይ የተወሰኑ ነጥቦችን በዳሰሳችን አንስተናል።

ጨዋታው በዋንጫ ፍክክሩ ውስጥ ካሉ ክለቦች መሀከል የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች የሚገናኙበት በመሆኑ ትኩረትን ይስባል። ምንም እንኳን ለተከታታይ ሳምንታት የውጤት ማሽቆልቆል ቢገጥመውም ከሰንጠረዡ አናት ሳይንቀሳቀስ የቆየው ደደቢት ጎንደር ላይ የገጠመው ሽንፈት ወደ ሁለተኛነት ዝቅ አድርጎታል። ስለሆነም ቡድኑ ከዚህም በላይ ላለመንሸራተት ቀጥተኛ ተፎካካሪው ከሆኑ ቡድኖች ጋር በሚገናኝባቸው እንደዛሬው አይነት ጨዋታዎች ላይ ሙሉ ነጥቦችን ለማግኘት መጣር ይኖርበታል። አንድ ተስተካካይ እና አንድ ያልተጠናቀቀ ጨዋታዎች የሚቀሩት መቐለ ከተማ ምንም እንኳን 6ኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጥም ከመሪው ጅማ አባ ጅፋር ጋር በነጥብ መስተካከል የሚያስችለውን ዕድል ይዟል። ነገር ግን ከዚያ አስቀድሞ ከአርባምንጩ ድል በኃላ የተቀዛቀዘውን ወቅታዊ አቋሙን ማስተካከል ይጠበቅበታል። ቡድኑ ከወልዲያ ነጥብ ከመጋራቱ በፊት በቅርብ ተፎካካሪው ጅማ አባ ጅፋር ከተሸነፈ በኃላ የሚያገኘው ሌላኛው በነጥብ ተቀራራቢ የሆነውን ተጋጣሚውን ማሸነፍ ካልቻለ የዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ለመቆየት ሊቸገር ይችላል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል አዲስ የጉዳት ዜና ያልተሰማ ሲሆን የደደቢቱ የፊት አጥቂ አቤል ያለው ከጉዳት መመለስ ግን እርግጥ አልሆነም። በመቐለ ከተማ በኩል ጨዋታው የሚያመልጠው ብቸኛ ተጨዋች የአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ያለበት የግራ መስመር ተከላካዩ አንተነህ ገ/ክርስቶስ እንደሆነም ታውቋል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


መቐለ ከተማ ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ለጥንቃቄ ቅድሚያ የሚሰጥ ቡድን በመሆኑ በዛሬውም ጨዋታ የተከላካይ መስመሩን እምብዛም ወደ መሀል ሜዳ ሳያስጠጋ በመስመር አማካዮቹ ብቻ የማጥቃት አማራጮችን በመፍጠር እንደሚጫወት ይጠበቃል። ጥሩ የመከላከል ሪከርድ ያለው ቡድኑ ለሁለቱ የተከላካይ አማካዮቹም የደደቢትን የመሀል ሜዳ የማጥቃት እንቅስቃሴ እና ወደ ጌታነህ ከበደ የሚላኩ ኳሶችን የማቋረጥ ዋነኛ ሀላፊነት እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ከዚህ አንፃር መሀል ለመሀል ቡድኑን ለማጥቃት አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል በንፅፅር የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ሊያገኙ የሚችሉት ደደቢቶች በዋነኛነት ወደ መስመር አጥቂዎቻቸው ከሚደርሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ስለመፍጠር ሊያስቡ ይችላሉ። ሆኖም ላለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው ደደቢት ከተጋጣሚው የመከላከል አደረጃጀት አንፃር ነገሮች ቀላል ላይሆኑለት ይችላሉ። በዛሬው ጨዋታም ደደቢት በነ የአብስራ ተስፋዬ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ እንዲሁም የሽመክት ጉግሳ እን ኤፍሬም አሻሞ የመስመር ጥቃት የተጋጣሚውን የመከላከል ክልል ሰብሮ ለመግባት የሚሞክርበት መቐለ ከተማም በመልሶ ማጥቃት ከሚያገኛቸው አጋጣሚዎች በአማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ኑሁ ፎሴይኒ ፍጥነት ታግዞ ወደ ጎል ለመድረስ የሚሞክርበትን የሜዳ ላይ ፉክክር የምንጠብቅበት ይሆናል።

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– መቐለ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈበት በሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ሁለቱ ክለቦች የተገናኙበት ጨዋታ በደደቢት 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

– ደደቢት ካለፉት ሰባት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ድል ሲቀናው በኒዚህ ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለውም አዳማን በረታበት ጨዋታ ላይ የተገኘቺውን የኤፍሬም አሻሞን ግብ ብቻ ነው።

– በሊጉ ጨዋታዎች ለመጨረሻ ጊዜ ካሸነፈ አንድ ወር ሊሞላው የተቃረበው መቐለ ከተማ እስካሁን ወደ አዲስ አበባ ስታድየም ከመጣባቸው 4 አጋጣሚዎች ውስጥ 2ቱን አሸንፏል።

ዳኛ

ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።