ሪፖርት | ወልዋሎ የሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ሶስት ነጥቡን አሳክቷል

በ21ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ በሜዳው አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ 3-0 በማሸነፍ የሁለተኛ ዙር የመጀመርያ 3 ነጥብ አሳክቷል።

ወልዋሎ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ከተረታው ስብስብ መካከል በማናዬ ፋንቱ ምትክ አብዱራህማን ፉሴይኒ በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ሲካተት በአርባምንጭ በኩል ደግሞ በመከላከያ ከተሸነፈው ስብስብ መካከል በአስጨናቂ ፀጋዬ እና ዘካርያስ ፍቅሬ ምትክ ወርቅይታደስ አበበ እና አለለኝ አዘነ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ተቀዛቅዞ እና ባልተሳኩ ረጃጅም ኳሶች ታጅቦ የተጀመረው ጨዋታው በመጀመርያዎቹ 10 ደቂቃዎች ለጎል የቀረበ ሙከራ ያልተስተናገደበት ሲሆን በተጫዋቾች መካከል የታየው ኃይል የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ ትኩረት የሳበ ትእይንት ነበር። የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም ቡድን ካልተሳኩ ረጃጅም ኳሶች ባሻገር ሁነኛ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ባለመፍጠሩ የተነሳ ሁለቱም በመስመር የተሰለፋት አጥቂዎች ስራ ፈትተው፣ አማካዮቹም በራሳቸው ሜዳ ተገድበው የቆዩ ቢሆንም አብዱራህማን ፉሴይኒ ከሌላው ጋናዊ አዶንጎ ጋር የፈጠሩት ጥምረት ለአርባምንጭ ተከላካዮች ፈተና ሲሆን ተስተውሏል። በ9ኛው ደቂቃም ከመሃል ሜዳ የተሻገረውን ኳስ ኦዶንጎ ተቆጣጥሮ ለአብዱልራህማን አቀብሎት አብዱራህማን በግሩም አጨራረስ ወልዋሎን መሪ ማድረግ ችሏል።

ጎሉ ከተቆጠረ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የገቡት አርባምንጮች ከ ወልዋሎ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢኖራቸውም ዝርግ በነበረው የተከላካይ መስመር እና በአማካዮች መሐል ያለው ርቀት የሰፋ በመሆኑና የቅብብል አማራጭ የሚፈጥር ተጫዋች ባለመኖሩ ከኋላ የሚመሰረቱ ቅብብሎቻቸው በቀላሉ ሲከሽፉ ተስተውለል። ወደፊት በሔዱባቸው አጋጣሚዎችም የጠራ የጎል እድል መፍጠር አልቻሉም። በጨዋታው ብቸኛ አጥቂ ሆኖ የተሰለፈው ብርሃኑ አዳሙ ከኳስ ውጭ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለወልዋሎ ተከላካዮች ፋታ የማይሰጥ እና አደረጃጀታቸውን የሚረብሽ ቢሆንም ከሌላው የቡድን አጋሮች ድጋፍ አለማግኘቱ እንዲባክን አድርጎታል። በተለይ በ17ኛው ደቂቃ ላይ ከመሃል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ የወልዋሎ ተከላካዮችን አለመናበብ ተጠቅሞ በግንባሩ በመግጨት ለጥቂት የወጣችበት ኳስ ለጥረቱ ማሳያ ነበረች።

ከ30 ደቂቃ በነበረው እንቅስቃሴ ሁለቱም ክለቦች ወደ ግብ ቶሎ ቶሎ በመድረስ በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም መካከል በ30ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ጋናዊው አብዱልራህማን ሞክሮ ፅዮን መርዕድ ያዳነበት እና በ34ኛው ደቂቃ ላይ ብርሃኑ አዳሙ የመታውን በረከት አማረ ያዳነበት ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች የተወሰደባቸው ብልጫ መልሰው ጫና መፍጠር የቻሉት ወልዋሎዎች በፕሪንስ እና አዶንጎ ተጨማሪ ጎል ለማግኝት ጥረት ቢያረጉም በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ፅዬን መርዕድ ጥረት ጎል ከመሆን ተርፈዋል። በተለይም በ38ኛው ደቂቃ ላይ ፕሪንስ 2 ተጫዋቾች አልፎ የሞከራት ኳስ የግብ ጠባቂው ብቃት ያሳየች ነበረች። በአርባምንጭ በኩልም በ42ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ አበራ ያደረጋት ሙከራ ተጠቃሽ ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ በተለይም በመጀመርያዎቹ 10 ደቂቃዎች ወልዋሎዎች ጫና ፈጥረው በመጫወት የጎል እድሎችን ፈጥረዋል። ለዚህም የመስመር አጥቂዎቹ ፕሪንስ እና አብዱራህማን የሜዳው ስፋት በመጠቀም የአርባምንጭ ተከላካዮች የመከላከል ቅርፅ እንዲበታተን ማድረጋቸው ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል። በዚህ ሒደትም በ55ኛው ደቂቃ አብዱራህማን ያሻማውን ኳስ ፕሪንስ አግኝቶ በአግባቡ በመጠቀም የወልዋሎን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ከጎሉ መቆጠር በኋላም ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉ ሲሆን በጨዋታው ኮኮብ ሆኖ የዋለው ሪችሞንድ አዶንጎ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታውን ኳስ ፅዮን መርዕድ እንደምንም አድኖበታል።

ከሁለተኛው ጎል መቆጠር በኋላ አርባምንጮች የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ይታይባቸዋል ተብሎ ቢጠበቅም ተቀይሮ በገባው ታሪኩ አማካኝነት ከርቀት ከሚሞክሩት ኳስ ውጪ የጠሩ የጎል እድሎች አልፈጠሩም። ይልቁንም የተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሐል በማስጠጋታቸው ከጀርባቸው ያለውን ሰፊ ክፍተት በመጠቀም ወልዋሎች ረጃጅም ኳሶችን ወደፊት በመጣል እድል ሲፈጥሩ ታይተዋል። በዚህም ተቀይሮ የገባው ማናዬ ፋንቱ በ82ኛው ደቂቃ ላይ ከመሐል ሜዳ በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ የወልዋሎን መሪነት ወደ 3-0 ማስፋት ችሏል። ጨዋታውም ተጨማሪ ሙከራ እና ጎል ሳይታይበት በዚሁ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ በሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ የመጀመርያ ሶስት ነጥቡን ያሳካው ወልዋሎ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ20 ነጥቦች ደረጃውን ወደ 12ኛ ከፍ ሲያደርግ አርባምንጭ ከተማ በ19 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

አስተያየቶች 

አስልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም

ዛሬ ውጤቱ ይገባናል። ከተጫዋቾች እስከ አመራሮች እንደ ክለብ በጋራ ነው የሰራነው። በጨዋታው ላይ ያደረግናቸው ቅያሪዎችም ውጤታማ ነበሩ። የዛሬው ጨዋታ ማሸነፋችን ከ 3 ነጥብም በላይ ትርጉም አለው። ክለባችን ውጤት ባጣበት ሰአት ከጎናችን ለነበሩ ደጋፊዎቻችን በሙሉ እናመሰግናለን።

* የአርባምንጭ አሰልጣኝ አስተያየት ባለመስጠታቸው ልናካትት አልቻልንም።