ሪፖርት | አርባምንጭ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመርታት እጅግ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክቷል

በ22ኛው ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ አርባምንጭ ላይ በተደረገ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመጀመርያው አጋማሽ ላይ በተቆጠሩ ጎሎች 3-0 አሸንፎ ወጥቷል።

ባለሜዳዎቹ አርባምንጮች በ21ኛ ሳምንት ከሜዳቸው ውጭ ወደ ዓዲግራት አቅንተው በወልዋሎ የ3-0 ሽንፈት ካስተናገዱበት ጨዋታ መልስ የቡድኑን ዋና አሰልጣኝ እዮብ ማለን አሰናብተው በምትኩ የቡድኑ ግብ ጠባቂ ጃክሰን ፊጣ እና ምክትል አሰልጣኙ ማትዮስ ለማ አማካኝነት ቡድኑን እየተመራ ሲገባ ተከላካዩ በረከት ቦጋለን በአንድነት አዳነ በመቀየር ለጨዋታው ቀርቧል። በአንፃሩ ፈረሰኞቹ በ21ኛው ሳምንት በሸገር ደርቢ ኢትዮዽያ ቡናን 1 – 0 ከረቱበት ስብስባቸው ምንም አይነት የተጨዋች ለውጥ ሳያደርጉ ለዛሬው ጨዋታ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ፌደራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው እና ረዳቶቻቸው በጥሩ መንገድ ጨዋታውን ተቆጣጥረው በመሩት በዚህ ጨዋታ ላይ የመጀመርያው ጎል ለመስተናገድ የፈጀው የዳኛው የጨዋታ መጀመር ፊሽካ ከተሰማበት በ1ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በዕለቱ በአርባምንጭ በኩል ቡድኑን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው አምበሉ አማኑኤል ጎበና በጥሩ ሁኔታ ከቀኝ መስመር እንዳለ ከበደ ያቀበለውን ኳስ ወደ ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት ወደ ጎል መሬት ለመሬት ሲመታው ኳሱን ተደርቦ ለማውጣት የሞከረው ሳላዲን በርጌቾን እግር ነክታ ሮበርት አዶንካራ መረብ ላይ አርፋለች።

በመጀመርያው ደቂቃ ላይ የተቆጠረችው ጎል በውጤት ቀውስ ውስጥ ለሚገኙት አርባምንጭ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረች ሲሆን ጨዋታው እምብዛም ማራኪ ባይሆንም ውጤት ይዞ ለመውጣት ከፈረሰኞቹ ይልቅ አርባምንጮች ላይ ትልቅ መነሳሳት ይታይ ነበር። ባልተሳኩ ቅብብሎች በሚቆራረጡ ኳሶች መሀል ሜዳ ላይ ብቻ ኳሱ እየተንሸራሸሩ ምንም የጎል ሙከራ በሁለቱም በኩል ሳንመለከት የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ቀጥሎ 31ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ተካልኝ ደጀኔ ያሻገረውን ተመስገን ካስቶሮ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ ኳሱን ከመሬት ጋር አንጥሮ ቢመታውም በግቡ ጠርዝ ለጥቂት የወጣው ሙከራ ብቻ የሚጠቀስ ነበር ።

38ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ አበራ ከመሀል ክፍል የተቀበለውን ኳስ ከግራ መስመር ወደ ሳጥኑ በመግባት የሮበርት ኦዶንካራን አቋቋም በማየት ባጠበበት በኩል ግሩም ጎል አስቆጥሮ አዞዎችን በሁለት ጎል ልዩነት እንዲመሩ አስችሏቸዋል ። ብዙም ሳይቆይ የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቂያ የዳኛው ፊሽካ ሲጠበቅ  በ44ኛው ደቂቃ አማኑኤል ጎበና አክርሮ የመታውን ተከላካዩ ሳላዲን በርጌቾ ኳስን በእጅ ነክቶታል በሚል የዕለቱ ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ፍ/ቅ/ምት ለአርባምንጭ ከነማ ሰተዋል ። የፈረሰኞቹም ተጨዋቾች የዳኛው ውሳኔ ተገቢ አይደለም በማለት የተቃወሙ ሲሆን እንዳለ ከበደ ፍ/ቅ/ምቱን ወደ ጎልነት ቀይሮ የአዞዎቹን የጎል መጠን ወደ ሦስት ከፍ አድርጎታል። ባለሜዳዎቹ አርባምንጮች ሦስቱንም ጎሎችን ባስቆጠሩባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ተጫዋቾቹ በአንድነት በመሆን ደስታቸውን የሚገልፁበት መንገድ አስገራሚ ነበር። በዚህም የመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታ መጠናቀቂያ ድረስ ፈረሰኞቹ በኩል አንድም ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ለጎል የቀረ ሙከራ ሳያደርጉ በአርባምንጭ 3-0 መሪነት እረፍት ወጥተዋል ።

ከእረፍት መልስ ፈረሰኞቹ በጊዜ የሦስት ተጨዋቾችን ለውጥ በማድረግ መሀሪ መናን በአበባው ቡጣቆ ፣ አቡበከር ሳኒን በሪቻርድ አፒያ እንዲሁም ጋዲሳ መብራቴን በአዳነ ግርማ በመቀየር ሙሉውን አጋማሽ በአርባምንጭ የሜዳ ክፍል ላይ አመዝነው በመጫወት ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ሆኖም እንደጥረታቸው የጎል አጋጣሚ ለመፍጠር እና በሜዳ ክፍላቸው በዝተው በጥብቅ ይከላከሉ የነበሩትን የአርባምንጭ ተጨዋቾችን አልፈው ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። አዳነ ግርማ እና ዛሬ የመጀመርያ ጨዋታውን በቅዱስ ጊዮርጊስ ማሊያ ያደረገው ጋናዊው አጥቂ ሪቻርድ አፒያ ከሚያደርጉት የግል ጥረት ውጭም የሚታይ የተደራጀ ነገር አልነበረም። ከዚህ በተለየ ግን በ66ኛው እና 75ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ አጋጣሚ ሁለት ጊዜ በመልሶ ማጥቃት የተሻገረለትን አጥቂው ብርሃኑ አዳሙ ከግብ ጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራ ጋር ብቻ ለብቻ ተገናኝተው ሮበርትን አልፎ ለማስቆጠር ሲሞክር ሳይጠቀምባቸው የቀሩ ኳሶች የአዞዎቹን የጎል መጠን ማስፋት የሚችልበት የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ።

በቀሩት ደቂቃዎች በተለያዩ ምክንያቶች ጨዋታው እየተቆራረጠ ቀጥሎ 90ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ሳላዲን በርጌቾ በደረቱ አልፎ በጥሩ ሁኔታ መትቶ የአርባምንጩ ግብጠባቂ ፅዮን መርድ በጥሩ ሁኔታ ያዳናት ኳስ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር። ጨዋታው በዚህ መልኩ በአርባምንጭ 3-0 ሲጠናቀቅ ያለፉትን ሁለት አመታት ሁለቱ ቡድኖች አርባምንጭ ላይ በሚገናኙበት አጋጣሚ ይፈጠር የነበረው ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ የሆነ ተግባር ሳይከሰት በጥሩ ድባብ በሰላም መጠናቀቅ ችሏል።

ውጤቱ ከ2007 በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመጀመርያ ጊዜ ያሸነፈው አርባምንጭ ደረጃውን ከግርጌ ወደ 12ኛ እንዲያሻሽል ሲረዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሪው ጅማ አባጅፋር ጋር ያለው ልዩነት የሚያጠብበትን እድል አምክኗል።

አሰልጣኞች አስተያየት 

ጃክሰን ፊጣ – አርባምንጭ ከተማ

በመጀመርያ ባመጣነው ውጤት የአርባምንጭ ደጋፊና ህዝብን በተጨዋቾቼ ስም እጅግ በጣም አመሰግናለው። ተጨዋቾቹንም ደጋፊዎቹን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እፈልጋለው ። በዛሬው ጨዋታ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል ፤ በደንብ ጠንክረን ሰርተን ነው ለዚህ ጨዋታ የቀረብነው ። በወልዋሎ ሦሰት ለዜሮ ተሸንፈን መጥተን የሊጉን ጠንካራ ቡድን ማሸነፍ መቻላችን የተጫዋቾቹን የአዕምሮ ጥንካሬ ነው የሚያሳየው። ገና ብዙ ጉዞ ይቀረናል ፤ ጀመርን እንጂ አልጨረስንም። ለቀጣይ ጨዋታዎች በሚገባ ተዘጋጅተን እንቀርባለን ።

ቫዝ ፒንቶ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ጨዋታው ሁለት መልክ ነበረው። በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ አልነበርንም። የመጀመርያው ጎል ተዘናግተን ተቆጠረ ፤ ሁለተኛውም በራሳችን ስህተት ጎል አስተናገድን ። የእኛ ተጨዋች በእጁ ያልነካውን ኳስ ዳኛው በስህተት ፍ/ቅ/ምት ተሰጠብን ። በአጠቃላይ የመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ አልነበርንም ። በሁለተኛው አጋማሽ ከአርባምንጭ በተሻለ የጎል አጋጣሚዎችን ፈጥረናል። ሆኖም ጎል አላስቆጠርንም ።  በጨዋታው ደስተኛ አይደለሁም ። በቀጣይ  አሁንም የዋንጫው ፉክክር ውስጥ ነው ያለነው ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ አለን። ሁሌም ለማሸነፍ ወደ ፊት እንሰራለን። ቀሪ ጨዋታዎችን በመርታት ዘድሮም ቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድሩ ቻምፒዮን ይሆናል ።