መቐለ ከተማ ለቀድሞ ተጫዋቾች የእውቅና ጨዋታ አዘጋጀ

መቐለ ከተማ ክለብ በትግራይ ክለቦች ከ2002 በፊት ለነበረው ውጤታማ የእግርኳስ እንቅስቃሴ የላቀ አስተዋፅኦ አድርገዋል ላላቸው ተጫዋቾች የእውቅና ጨዋታ ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

ክለቡ በ18ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ ቀደም ብሎ 07:00 በሚጀምረው ጨዋታ ላይ ለጉና ንግድ እና ትራንስ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ አገልግሎት ያበረከቱ ተጫዋቾች ይታሰቡበታል።

በ1997 በፕሪምየር ሊጉ 2ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ትራንስ ኢትዮጵያ እና በ1991 በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ተካፍሎ በዛንዚባር ፖሊስ ተሸንፎ ከውድድር የወጣው ጉና ንግድ ውስጥ ተሳትፎ ባደረጉ ተጫዋቾች እና ሌሎች ተጫዋቾች መካከል ጨዋታ የሚደረግ ሲሆን በጨዋታው ከተጋበዙ የቀድሞ ተጫዋቾች መካከል ለሁለት አስርት አመታት እግርኳስን የተጫወተው የቀድሞ የትራንስ ኢትዮጵያ ተጫዋች ገረሱ ሸመና በከተማው ነዋሪዎች ደማቅ አቀባባል ተደርጎለታል።

ጨዋታው ለቀድሞ ተጫዋቾች እውቅና ከመስጠት ባለፈ ለአዲሱ ትውልድ ልምዳቸው እንዲያካፍሉ እና በክልሉ የተፈጠረው የስፖርት መነቃቃትን ለማስቀጠል በማሰብ የተዘጋጀ እንደሆነ  ክለቡ አስታውቋል።