ቻምፒየንስ ሊግ | ኬሲሲኤ፣ ማዜምቤ እና ምባባኔ ስዋሎስ ድል ቀንቷቸዋል

የካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ማክሰኞ እና ረቡዕ በተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች ሲደረጉ ኬሲሲኤ፣ ምባባኔ ስዋሎስ፣ ቲፒ ማዜምቤ፣ ኤስፔራንስ፣ ኤትዋል ደ ሳህል፣ ዋይዳድ እና ኤምሲ አልጀር ወሳኝ ሶስት ነጥቦችን አግኝተዋል፡፡

ምድብ ሀ

በዚሁ ምድብ ካምፓላ ላይ በተደረገ ጨዋታ ኬሲሲኤ በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ የቻምፒየንስ ሊግ ሶስት ነጥቡን አሳክቷል፡፡ የሉጎጎው ክለብ የስምንት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኑን አል አህሊን 2-0 አሸንፏል፡፡ የድል ግቦቹን ሳዳም ጁማ እና አምበሉ ቲሞቲ አዎኒ ነበር ያስገኙት፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የአህሊው አሰልጣኝ ሆሳም ኤል-ባድሪ ከክለብ አሰልጣኝነታቸው ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል፡፡

ቱኒዝ ላይ ኢትዮጵያዊው አርቢትር ባምላክ ተሰማ በመራው ጨዋታ ኤስፔራንስ የቦትስዋናውን ታውንሺፕ ሮለርስን 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፋል፡፡ ለቀይ እና ወርቃማዎቹ ግቦች የሱፍ ቤልአሊ፣ አኒስ ባድሪ እና ቢሊል መጅሪ ሲያስቆጥሩ ለታውንሺፕ ሰጎሌም ቦይ ከመረብ አዋህዷል፡፡

ምድቡን ኤስፔራንስ በ4 ነጥብ ይመራል፡፡

ምድብ ለ

ቲፒ ማዜምቤ አሁን በአሸናፊነቱን ቀጥሏል፡፡ የሉቡምባሺው ክለብ ወደ ሞሮኮ ተጉዞ ዲፋ ኤል ጃዲዳን 2-0 ረቷል፡፡ ቤን ማላንጎ እና አብዱላሂ ሲሶኮ ማዜምቤ ምድቡን እንዲመራ ያስቻሉትን ግቦች አስገኝተዋል፡፡

ሁለት የአልጄሪያ ክለቦችን ባገናኘው ጨዋታ ኤምኢ አልጀር ከሜዳው ውጪ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ ኢኤስ ሴቲፍን 1-0 አሸንፏል፡፡ አሚር ካራዊ ለአልጀርሱ ሃያል ክለብ ወሳኝ ሶስት ነጥብን ያስገኘች ግብ በ89ኛው ደቂቃ ከመረብ አዋህዷል፡፡
ምድቡን ቲፒ ማዜምቤ በ6 ነጥብ ይመራል፡፡

ምድብ ሐ

የወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒዮን ዋይዳድ ካዛብላንካ በስታደ መሃመድ አምስተኛ ኤኤስ ቶጎ ፖርትን አስተናግዶ 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ መሃመድ ኦንዠም፣ ነኢም አረብ እና መሃመድ ኤል ናሂሪ የግቦቹ ባለቤቶች ናቸው፡፡

በዚሁ ምድብ ሊደረግ የነበረው የሆሮያ እና ማሜሊዲ ሰንዳውንስ ጨዋታ የደቡብ አፍሪካው ቻምፒዮን ከባርሴሎና ጋር ረቡዕ በነበረው የወዳጅነት ጨዋታ ምክንያት ለመጪው ማክሰኞ ተሸጋግሯል፡፡

ምድቡን ዋይዳድ በ4 ነጥብ ይመራል፡፡

ምድብ መ

የመጀመሪያ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኘው የስዋቲኒው ክለብ ምባባኔ ስዋሎስ ባልተጠበቀ የቻምፒየንስ ሊግ ጉዞ ላይ ተግኝቷል፡፡ የአንጎላውን ፕሪሜሮ አውጉስቶን አስተናግዶ በፊሊክ ባድንሆረስት ብቸኛ ግብ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በቱኒዚያ ዋንጫ ፍፃሜ በክለብ አፍሪካ 4-1 የተረመረመው ኤትዋል ደ ሳህል ዜስኮ ዩናይትድን 2-1 ረቷል፡፡ አላያ ብሪጊ እና አምር ማሪ ለሶሱ ክለብ ግቦቹን ሲያስቆጥሩ የንዶላውን ክለብ ከመሸነፍ ያላዳነች አንድ ግብ ላዛረስ ካምቦሌ በ90ኛው ደቂቃ የኤትዋልን ግብ ጠባቂ ስህተት ተጠቅሞ አስገኝቷል፡፡

ምድቡን ኤትዋል ደ ሳህል እና ምባባኔ ስዋሎስ በእኩል 4 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ይመሩታል፡፡

የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ውጤቶች

ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦውቶሪቲ (ዩጋንዳ) 2-0 አል አህሊ (ግብፅ)
ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ (ቱኒዚያ) 4-1 ታውንሺፕ ሮለርስ (ቦትስዋና)
ዲፋ ኤል ጃዲዳ (ሞሮኮ) 0-2 ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)
ኢኤስ ሴቲፍ (አልጄሪያ) 0-1 ሞውሊዲያ ክለብ ደ አልጀር (አልጄሪያ)
ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ 3-0 ኤኤስ ቶጎ ፖርት (ቶጎ)
ምባባኔ ስዋሎስ (ስዋቲኒ) 1-0 ክለብ ዴፖርቲቮ ፕሬሜሮ አውጉስቶ (አንጎላ)
ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ) 2-1 ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ)