ኮንፌድሬሽን ዋንጫ | የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ተደርገዋል

በካፍ ቶታል ኮንፌድሽን ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ቀጥለው ሲደረጉ ቪታ ክለብ፣ ሬኔሳንስ በርካን እና ካራ ብራዛቪል ድል ሲቀናቸው አምስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል፡፡

ምድብ ሀ

ኪንሻሳ ላይ ኤኤስ ቪታ የኮትዲቯሩን አሴክ ሚሞሳስን ገጥሞ 3-1 አሸንፏል፡፡ ሚሞሳስ በግባግኖን ባዴ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ በመጀመሪያው አጋማሽ መሪነቱን ቢጨብጥም በሁለተኛው 45 ክሪስቲያን ንጉዲካማ አከታትሎ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች እና በሙዚንጋ ንጎንዳ ተጨማሪ ግብ ቪታ 3-1 አሸንፏል፡፡

ዶርማ ላይ የጋናው አዱአና ስታርስ ሶስት ግዜ ከኋላ ተነስቶ ከሞሮኮው ራጃ ካዛብላንካ ጋር 3-3 ተለያይቷል፡፡ ራጃዎች በመሃሙድ ቤንሃሊብ የ11ኛ ደቂቃ ግብ መሪ ሲሆኑ ኦባ ኡሊትች ከ10 ደቂቃ በኃላ አዱአናን አቻ አድርጓል፡፡ ኮንጎዋዊው ሌማ ማቢዲ እረፍት ከመውጣታቸው በፊት የራጃን መሪነተ ሲመልስ ካሌብ አማንካዋ አዲአናን ዳግም አቻ አድርጓል፡፡ ቤንሃሊብ እና ናትናኤል አሰሞሃ ተጨማሪ ግቦችን አስቆጥረው ጨዋታው 3-3 ተጠናቋል፡፡

ቪታ ክለብ ምድቡን በ4 ነጥብ ይመራል፡፡

ምድብ ለ

የሞዛምቢኩ ዩዲ ሶንጎ የሞሮኮው ሬኔሳንስ በርካንን አስተናግዶ 2-0 ተሸንፏል፡፡ የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ኮከብ ግብ አግቢ የነበረው አዩብ ኤል ካቢ የበርካንን ሁለት ግቦች ከእረፍት መልስ አስቆጥሯል፡፡

ኦምዱሩማን ላይ የሱዳኑ አል ሂላል እና የግብፁ አል መስሪ 1-1 ተለያይተዋል፡፡ ኢስላም ኢሳ የፖርት ሳኢዱን ክለብ በ10ኛው ደቂቃ መሪ ሲያደርግ የሂላሉ ተከላካይ ኤል ጣሂል ሃሰን በሰራው ጥፋት በ26ኛው ደቂቃ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡ በ10 ተጫዋቾች አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ግዜ ለመጫወት የተገደደው ሂላል በጆቫኒ ማራናሆ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡

ምድቡን ሬኔሳንስ በርካን በ6 ነጥብ ይመራል፡፡

ምድብ ሐ

የኮንጎ ሪፐብሊኩ ካራ ብራዛቪል በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ውስጥ ባስቆጠራቸው ሶስት ግቦች የናይጄሪያውን ኢኒየምባን 3-0 ረቷል፡፡ በ14፣ 17 እና 19ኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠሩትን ግቦች ራሲን ሉዋምባ፣ ካቡዌ ኪቩቱካ፣ ዲቻ ቦማንያ አስገኝተዋል፡፡

ባማኮ ላይ የማሊው ጆሊባ እና የኮትዲቯሩ ዊሊያምስቪል 1-1 ተለያይተዋል፡፡ ማማዱ ሲሴ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረው ግብ ባለሜዳው ቢመራም የግብ ጠባቂ ስህተት ታክሎበት የተገኘውን እድል ጃን ፍራንሲስ ዳ ዊሊያምስቪልን አቻ አድርጓል፡፡

ዋሊያምስቪል በ4 ነጥብ ምድቡን እየመራ ይገኛል፡፡

ምድብ መ

ዳሬ ሰላም ላይ የታንዛኒያ አዛም ፕሪምየር ሊግ ክብሩን ለከተማ ተቀናቃኙ ሲምባ አሳልፎ የሰጠው ያንግ አፍሪካንስ ከሩዋንዳው ራዮን ስፖርትስ ጋር ተጫውቶ ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ በጨዋታው ላይ ራዮን ከያንጋ በተሻለ የግብ እድሎችን ቢፈጥርም ግብ ለማስቆጠር ግን አልቻለም፡፡

ናይሮቢ ላይ ጎር ማሂያ የአልጄሪያውን ዩኤስኤም አልጀርን አስተናግዶ 0-0 ተለያይቷል፡፡ በግዙፉ ካሳራኒ በተካሄደው ጨዋታ ሃይለኛ ዝናብ መዝነቡ ለሁለቱም ክለቦች አስቸጋሪ ግጥሚያ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ጎር ጆሽ አቦንጎ በሁለት ቢጫ በ55ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ በመውጣቱ በ10 ተጫዋች ጨዋታውን ለመጨረስ ተገዷል፡፡

ዩኤስኤም አልጀር ምድቡን በ4 ነጥብ ይመራል፡፡

የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች አጠቃላይ ውጤቶች
ኤኤስ ቪታ ክለብ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) 3-1 አሴክ ሚሞሳስ (ኮትዲቯር)
አዱአና ስታርስ (ጋና) 3-3 ራጃ ክለብ አትሌቲክ (ሞሮኮ)
ዩዲ ዱ ሶንጎ (ሞዛምቢክ) 0-2 ሬኔሳንስ በርካን (ሞሮኮ)
ካራ ብራዛቪል (ኮንጎ ሪፐብሊክ) 3-0 ኢኒየምባ ኢንተርናሽናል (ናይጄሪያ)
ጆሊባ ኤሲ (ማሊ) 1-1 ዊሊያምስቪል (ኮትዲቯር)
ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) 0-0 ራዮን ስፖርትስ (ሩዋንዳ)
ጎር ማሂያ (ኬንያ) 0-0 ዩኒየን ስፖርቲቭ መዲና ደ አልጀር (አልጄሪያ)