ፕሪምየር ሊግ | የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ – ክፍል 2 

ነገ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሚከናወኑ 8 የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መሀከል በሰበታ ፣ ሶዶ እና ድሬደዋ የሚደረጉት ሶስት ጨዋታዎች የዛሬ ክፍል ሁለት ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችን ትኩረት ሆነዋል።

               
ወልዲያ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ዋንጫን ሩብ ፍፃሜ ለመቀላቀል ተገናኝተው የነበሩት ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ደግሞ መጫወቻ ቦታቸውን ወደ ሰበታ ቀይረው ዳግም ይገናኛሉ። ኢትዮጵያ ቡና በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ኮስታራ ተሳታፊ ሊያደርጉት ይችሉ ነበሩትን የቀደሙ ዕድሎችን መጠቀም ባለመቻሉ ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ የማግኘት ግዴታ ይኖርበታል። ከየካቲት ወር መገባደጃ በኃላ ወደ አሸናፊነት መመለስ ያልቻለው ወልዲያም በሊጉ ግሬጌ የሚገኝ በመሆኑ ከበላዩ ያሉት ክለቦች ልዩነቱን ከአንድ ጨዋታ ውጤት በላይ ከማስፋታቸው በፊት ቀድሞ አቋሙን ማስተካከል ይጠበቅበታል። በዚህም መሰረት የሰበታው ጨዋታ መልካም እንቅስስሴ እንደታየበት የአርቡ ጨዋታ ሁሉ ሁለቱም ለመሸናነፍ የሚፉለሙበት እንደሚሆን ይታሰባል።

የአንድ አመት ቅጣት ከተላለፈበት ብሩክ ቃልቦሬ እና የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኘው ሰለሞን ገብረመድህን ውጪ የወልዲያ ስብስብ ለጨዋታው ብቁ ሲሆን አስናቀ ሞገስን በቅጣት የሚያጣው ኢትዮጵያ ቡና ቀሪዎቹ ተጨዋቾቹ በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ።

ባሳለፍነው አርብ የተደረገው ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች የተጋጣሚያቸውን ደካማ ጎኖች ለይቶ ለማወቅ እና ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን ዕቅዶች ለመንደፍ ሰፊ ዕድል እንደሚሰጣቸው ይታመናል። በወልዲያ በኩል ለመጀመሪያ ጊዜ ቡድኑን እንደሚመሩ የሚጠበቁት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ወልዲያ መሀል ሜዳ ላይ ሲወሰድበት ከታየው የቁጥር ብልጫ ይፈጥርበት የነበረውን ጫና ለመቀለስ ከሁለቱ አጥቂዎቻቸው አንደኛውን ለአማካይ ክፍሉ ቀርቦ እንዲጫወት ሊያረጉ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል። የኢትዮጵያ  ቡና የመሀል ተከላካዮች ጥምረት ድክመትንም ለዓንዷለም ንጉሴ በሚጣሉ ቀጥተኛ ኳሶች እና በድንገተኛ ጥቃቶች ይፈትናሉ ተብሎም ይጠበቃል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል የተመጠነ የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ተሳትፎ እንዲኖር በማድረግ ለመልሶ መጠቃት በማያጋልጥ መልኩ የሜዳውን ስፋት በመጠቀም እና የወልዲያን የኃላ መስመር መሀል ክፍተት እንዲፈጠር በማስገደድ በአጫጭር ቅብብሎች የማጥቃት ዕቅድ አዋጭ ይሆናል። ለዚህም የቡድኑ ፈጣሪ አማካዮች የዳንኤል ደምሴ እና ሀብታሙ ሸዋለምን ጥምረት በማለፍ ወደ ሳሙኤል ሳኑም የሚያደርሷውቸን ቅብብሎች በአግባቡ መከወን ይኖርባቸዋል።  

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ወልዲያ እና ኢትዮጵያ ቡና 5 ጊዜ ተገናኝተው ወልዲያ አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ቡና 3 ጊዜ ድል ቀንቶታል። በአንድ አጋጣሚ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ወልዲያ 6 ጎል ሲያስቆጥር ቡና 11 አስቆጥሯል። 

– በሁለተውኛ ዙር አንድ ነጥብ ብቻ ያሳካው ወልዲያ ግብ ሳያስተናግድ የወጣውም አንዱን ነጥብ ባሳካበት እና 0 0 በተጠናቀቀው የመቐለ ጨዋታ ብቻ ነው።

– በመጨረሻዎቹ ሁለት የሊጉ ጨዋታዎቹ ግብ ማስቆጠር ያልቻለው ኢትዮጵያ ቡና ከመጨረሻ አራት ጨዋታዎቹ አንዱን ሲያሸንፍ  ሁለቴ ሽንፈት ገጥሞታል።

ዳኛ

– ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን መሪነት የሚከናወን ይሆናል።

ድሬደዋ ከተማ ከ መከላከያ

ይህ ጨዋታ ከመከላከያ በላይ ለባለሜዳው ድሬደዋ እጅግ አስፈላጊ ነው። በተስተካካይ ጨዋታ ወላይታ ድቻን በመርታት ከወራጅ ቀጠውና በአንድ ነጥብ መውጣት የቻለው ድሬደዋ ወደ ታች የማሽቆልቆል ስጋቱ አሁንም ያለ በመሆኑ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ግድ ይለዋል። እስካሁን ተከታታይ ድል አሳክቶ የማያውቀው ድሬደዋ ይህን ማድረግ ከቻለ መጠነኛ እስትንፋስ የሚያገኝ ይሆናል። በ28 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መከላከያ ግን ሊጉ ከመቋረጡ በፊት የነበረውን አስደናቂ አቋም ለመቀጠል ቢጫወትም ከመውረድ ስጋት መራቁ እና ወደ መሪዎች ለመቅረብ ካለው ዝቅተኛ ዕድል አንፃር በጨዋታው አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ አይገባም። 

የድሬደዋ ከተማው ጋናዊ አማካይ ሚካኤል አካፉ እጁ ላይ ከገጠመው ጉዳት ያላገገመ ሲሆን ዘነበ ከበደ እና ያሬድ ታደሰም ለጨዋታው መድረሳቸው  አጠራጣሪ ሲሆን በመከላከያ በኩል ሳሙኤል ሳሊሶ በምግብ መመረዝ  የተሻ ግዛው ደግሞ በፍርድ ቤት ቀጠሮ ምክንያት ወደ ድሬደዋ አላመሩም።

ሁለቱም ቡድኖች በርከት ያሉ የአማካይ መስመር ተጨዋቾቻቸው በማጥቃት ላይ እንዲሳተፉ ፍቃድ የሚሰጡ በመሆናቸው በቦታው የሚኖረውን ፍልሚያ እንድንጠብቀው ያደርጋል። በግል ብቃትም ሆነ በቡድን ውህደት እየተሻሻለ የመጣው መከላከያ የኳስ ፍሰቱን እስከአጥቂዎቹ ድረስ በስኬት ለማድረስ ዳዊት እስጢፋኖስ በሁለቱ የድሬ የተከላካይ አማካዮች ፊት ነፃ ሆኖ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ማድረስ የሚችልበትን ክፍተት መፍጠር ይኖርበታል። እንደሁኔታው በአምስት ወይም በአራት አማካዮች የሚጠቀመው መከላከያ ጥሩ ንቃት ላይ ከሚገኙት የመስመር ተሰላፊዎቹም ሲያገኝ የሚታየው አገልግሎት ተጠቃሚ እያደረውገ ይገኛል። በሜዳው ቁመት መሀል ለመሀል ጥቃቶችን ለመመከት እምብዛም የማይቸገሩት ድሬዎች የመከላከያን አማካዮች እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ወደ ፊት አጥቂያቸው የሚልኳቸው ኳሶች ላይ እምነታውቸን ያሳድራሉ። ሆኖም ፊት ላይ ያለው የአጨራረስ ችግር ቡድኑን ሊያስቸግረው እንደሚችል ቢታሰብም በዛው ልክ ደግሞ በጨዋታው ቀድሞ ግብ ካስቆጠረ ውጤት በማስጠበቁ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ይገመታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ድሬዳዋ ከተማ እና መከላከያ ከዚህ ቀደም 13 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን መከላከያ ከፍተኛ የበላይነት አለው። ድሬዳዋ አንድ ጊዜ ብቻ ሲያሸንፍ መከላከያ 9 ጊዜ አሸንፏል። ቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተለያዩባቸው ነበሩ። መከላከያ 25 ፣ ድሬዳዋ 10 ጎሎች አስመዝግበዋል።

– ድሬዳዋ ላይ በተከናወኑ 6 ጨዋታዎች ባለሜዳው አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ መከላከያ 2 ጊዜ አሸንፎ በቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

– ድሬዳዋ መከላከያን ለመጀመርያም ለመጨረሻም ጊዜ ያሸነፈው በ2001 የውድድር ዘመን ነበር።

– ድሬደዋ ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ ሜዳው ላይ ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ሶስቱን አሸንፎ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል።

– መከላከያ ዘንድሮ ከሜዳው ከወጣባቸው ሰባት አጋጣሚዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ ሶስቴ ሽንፈት ገጥሞት በሁለት አጋጣሚዎች  አንድ ነጥብ ይዞ ተመልሷል።

ዳኛ

– ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የሚመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው ነው።

ወላይታ ድቻ ከ ሲዳማ ቡና

በብዛት ከሚነግስበት ውጥረት አንፃር ስጋት ከሚያጭሩ የሊጉ መርሀግብሮች መሀከል አንዱ የሆነው የወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በሜዳ ላይም ጠንካራ ፉክክር እንደሚያስተናግድ ይጠበልቃል። በኩል 27 ነጥቦች የሻምፒዮንነት ፉክክር ውስጥም ሆነ በሊጉ የመቆየት ትግል ውስጥ የማይገኙት ሁለቱ ክለቦች ጨዋታውን በአሸናፊነት ለመወጣት ምክንያት የሚሆናቸው በመሀላቸው ያለው የደርቢነት ስሜት ብቻ ይመስላል። ከሶዶ ውጪ ሰበታ ላይ ብቻ ድል የቀናው ወላይታ ድቻ ከደካማው ወቅታዊ አቋሙ ለማገገም ወደሜዳው መመለሱ ተጠቃሚ ያደርገዋል። ከተጋጣሚው በተለየ ደርሶበት ከነበረው የውጤት መንሸራተት ያገገመው ሲዳማ ቡና በበኩሉ በውድድር ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ካሳካው ተከታታይ ድል በኃላ ወደ ሶዶ የሚያመራ ይሆናል።

በክለቡ ቅጣት ከተላለፈበት የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ወንደሰን ገረመው ውጪ ቀሪዎቹ የሁለቱም ተጋጣሚ ክለቦች ተጨዋቾች ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ሆነው ለጨዋታው ይደርሳሉ።

በሁለቱም ሽግግሮች ወቅት የነበረውን ጥንካሬ እያጣ የመጣው ወላይታ ድቻ በተለይ ግቦችን በማስቆጠሩ በኩል የመስመር አማካዮቹ ፈጣን የማጥቃት ተሳትፎ በእጅጉ ያስፈልገዋል። የፊት አጥቂው ጃኮ አራፋት ከሳጥን ውጪ በመውጣት ከአማካይ ክፍሉ ጋር ለመገናኘት የሚያደርገውን ጥረት ማዕልከ ባደረገ መልኩ በሁለቱ መስመሮች የሚሰለፉት የድቻ አማካዮች በመከላከል ሂደት ከሚሰጡት ሽፋን ባለፈ የሲዳማን የመስመር ተከላካዮች አልፈው መግባት ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ ከአማካይ መስመር ተሰላፊዎቹም ግቦችን ማግኘት ስለሚኖርበት በዛብህ መለዮ እና አብዱልሰመድ ዓሊ ዘግይተው ወደ ሲዳማ ሳጥን ሲደርሱ የሚገኟቸውን ዕድሎች ወደግብ መቀየር ይኖርባቸዋል። በሲዳማ በከል ግቦችን ወደ ማስቆጠሩ የተመለሰው  አማካይ ወንድሜነህ ዓይናለም እና አጣማሪው ፍፁም ተፈሪ ፈጣኖቹ የቡድኑ የመስመር አጥቂዎች አጥብበው ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክልል መግባት እንዲችሉ በመከላከሉ ጥሩ የአማካይ ክፍል ዕገዛን ከሚያገኘው ኃይማኖት ግርማ ፊት የቁጥር ብልጫ እንዳይወሰድባቸው የሚያደርግ የጨዋታ ዕቅድ ለሲዳማዎች ወሳኝ ይሆናል። የቡድኑ የተሻለ የማሸነፍ መንፈስ ላይ መገኘት በራሱ የፊት አጥቂዎቹ ላይ የሚፈጥረው በራስ መተማመን ከድቻ የኃላ መስመር ተሰላፊዎች ጋር ሲገናኙ አደጋ ለመፍጠር የሚኖረው እገዛም ቀላል አይሆንም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ወላይታ ድቻ ከ ሲዳማ ቡና 9 ጊዜ ተገናኝተው ድቻ አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ፣ ሶስት ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ ቡና ደግሞ 5 ጊዜ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ድቻ 4  ሲዳማ ደግሞ 10 ጎሎች አስቆጥረዋል።

– 3 ጎሎች በቻ በተቆጠሩባቸው ድቻ ሜዳ ላይ በተደረጉ 4 ጨዋታዎች ባለሜዳው አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ 3 ጨዋታዎችን አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ ቡና ግን ከሜዳው ውጪ አሸንፎ አያውቅም።

– ባለፉት 5 የእርስበእርስ ግንኙነቶች ድቻ በሲዳማ ላይ ድል ማስመዝገብ አልቻለም።

– ወላይታ ድቻ በሁለተኛ ዙር ሜዳው ላይ ካስተናገዳቸው አራት ጨዋታዎች 8 ነጥቦችን ሲሰበስብ ሽንፈት ሳይገጥመው ነበር።

– በሁለተኛው ዙር ሶስቴ ከሜዳው የወጣው ሲዳማ አንዴ ሲያሸንፍ ግብ ያላስቆጠረባቸው የተቀሩትን ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፏል።

ዳኛ

– ይህን ጨዋታ ፌደራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።