የወልዲያ እና ጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ይካሄዳል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ወልዲያ ከ ጅማ አባጅፋር ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመደበኛነት ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ወልዲያ ላይ የነበረ ቢሆንም ክለቡ 3 በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ከ500 ኪ/ሜ ርቀት በላይ በሚገኝ ሜዳ እንዲያከናውን በመወሰኑ ምክንያት ይህን ጨዋታም በቅጣት ውሳኔው መሠረት የሚያደርግ ይሆናል።

በቅጣቱ ምክንያት ወልዲያ ከ ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ሰበታ ላይ ማከናከኑ የሚታወስ ሲሆን ቀጣይ የሜዳ ጨዋታው በ25ኛው ሳምንት ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ቢሆንም ጨዋታው ቀድሞውኑም በአዲስ አበባ ስታድየም እንዲደረግ የተወሰነ በመሆኑ በዚህ የውሳኔ ዝርዝር ውስጥ አልተካተተም። በዚህም ምክንያት በ27ኛው ሳምንት ከጅማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ቅጣቱ ተግባራዊ የሚሆንበት የመጨረሻ መርሐ ግብር ይሆናል ተብሏል።

በመሆኑም በወልዲያ እና ጅማ አባ ጅፋር መካከል የሚደረገው የ27ኛ ሳምንት ጨዋታ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሰኔ 6 ደደቢት ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሚገናኙበት ጨዋታ አስቀድሞ የሚካሄድ ይሆናል።