ሪፖርት | ፋሲል ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

በ24ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰኞ 9፡00 ላይ እንዲካሄድ ታስቦ በዝናብ ምክንያት አንድ ቀን ተራዝሞ ዛሬ ከጠዋቱ አራት ስአት ላይ የተደረገው የፋሲል ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።

ፋሲል ከተማ በ23ኛው ሳምንት ወደ ሀዋሳ ይዞ ከሄደው የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሰይድ ሁሴን ፣ ያስር ሙገርዋ እና ሀሚስ ኪዛን አሳርፎ በምትካቸው ፣ አብዱርሀማን ሙባረክ እና ፍሊፕ ዳውዝን አሰልፏል። መከላከያን ሜዳው ላይ አስተናግዶ ድል ያደረገው ድሬዳዋ በበኩሉ በጉዳት ባጣው ሀብታሙ ወልዴ ምትክ ሳውሬል ኦልሪሽን በመጀመሪያው አሰላለፍ ውስጥ አካቶ ወደ ሜዳ ገብቷል።

ባለሜዳዎቹ ፋሲል ከተማዎች ተጭነው በተጫወቱበት የመጀመሪያ አጋማሽ ፊሊፕ  ዳውዝ በ7ኛው ደቂቃ ከሰይድ ሁሴን ከርቀት የተሻገረለትን መቆጣጠር ባለመቻሉ የተገኝውን አጋጣሚ አምክኖታል እንዲሁም ሰንደይ ምትኩ በ11ኛው ደቂቃ ከኄኖክ ገምቴሳ የተሻማ የቅጣት ምት በጭንቅላቱ ገጭቶ ውደ ውጪ ወትቶበታል። በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረው ኤፍሬም አለሙ ከርቀት ከሞከራቸው ኳሶች በስተቀር ፋሲሎች የድሬዳዋ ከተማን የተከላካይ መስመር ሰብረው ለመግባት ሲቸገሩ ተስተውለዋል። በጥንቃቄ በመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት እድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ በነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በኩል አትራም ኩዋሜ በ30ኛው ደቂቃ ከርቀት የሞከረው እና በ40ኛው ደቂቃ ከበረኛ ተገናኝቶ ግብ ጠባቂ ያዳነበት ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ የታዩ የድሬዎች ሙከራ ናቸው።

በቀዝቃዛው የአየር ሁኔታ የተጀመረው የሁለተኛው አጋማሽ ግጭት የበዛት ነበር። በዚህም ምክንያት ተደጋጋሚ የዳኛ ፊሽካ እና የጨዋታ መቆራረጥ ታይቶበታል። ፋሲል ከተማዎች በኩል ከታዩ ሙከራዎች በ48ኛው ደቂቃ ኄኖክ ገምቴሳ ኤፍሬም አለሙ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኝ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል የተጠጋ ቅጣት ምትን ሲያመክን በ67ኛው ደቂቃ በአብዱራህማን ሙባረክ ከራምኬል ሎክ የተሻገረለት እና ያልተጠቀመበት ሌላው የሚየስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በ71ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ ከርቀት አክርሮ የመታው እና በ85ኛው በመሀመድ ናስር ራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኝውን የቅጣት ምት ሳይጠቀምበት የቀረበት አጋጣሚም ተጠቃሽ ነው።  ፋሲል ከተማ የድሬዳዋን ግብ ለመድፈር የሚያስችሉ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልሉ አቅራቢያ በርካታ የቆሙ ኳሶችን ማግኘት ቢችልም ወደ ግብ መቀየር ግን ተስኖታል። ከዚህ ውጪ ቡድኑ በጭማሪ ደቂቃ በይስሀቅ መኩሪያ ጥሩ ሙከራዎችን መድረግ ቢችልም ሶስት ነጥቡን ለመጋኘት ግን በቂ አልነበረም። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ከፊት መስመር ባሉት በዮሴፍ ዳሙዬ እና ኩዋሜ አትራም በመልሶ ማጥቃት ወደፊት መጠጋት የቻሉባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም ደህና ሙከራ ማድረግ ግን አልቻሉም። ያም ቢሆን ድሬድዋ ከተማዎች ከወረጅ ቀጠና ለመራቅ በጥንቃቄ ተከላክለው ከሜዳቸው ውጭ ነጥብ ተጋርተው መውጣት አልተሳናቸውም። በውጤቱም ሁለቱም ክለቦች ደረጃቸውን ከነበሩበት በአንድ ማሻሻል ችለዋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት 

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – ፋሲል ከተማ

ጨዋታው ጥሩ ነበር። ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ጥረት አድርገናል ፤ ማሽነፍ ነበር አላማችን ፤ አልተሳካም። ግብ እንዳናስቆጥር  ምክንያት የሆነብን የነሱ የመከላከል ጥንካሬ ነው። ሁለት የተከላካይ አማካይ ይዘው ነው የገቡት። በተጨማሪም የነሱ ተጫዋቾች በዞን በመከላከል ላይ ጥሩ ናቸው። አጨዋወታቸው ክፍተት የሚሰጥ አይነት አይደለም። በዚህ ምክንያት ግብ እንዳናይ አድርጎናል። በዛሬው ጨዋታ አላማ አድርገን የገባነው 36 ነጥብ ላይ መድረስን ነበር። ቢሆንም ከዚህ በኃላ እስከ መጨረሻው በውጤት ስሌት አሸናፊው እስኪታወቅ ተስፋ አንቆርጥም ።

አሰልጣኝ ስምኦን ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ

እኛ ወደዚህ የመጣነው ለማሸነፍ ወይም አቻ ለመውጣት ነበር። የመጣንበትን በግማሽ አሳክተናል።  ይህ የሆነው በተጨዋቾቻችን ቆራጥነት ነው። በአሁኑ ስአት ቡድኔ ጥሩ መነሳሳት ላይ ነው። በሜዳችን ምንፈልገውን ነገር እያሳካን ነው። ቢሆንም በአሁኑ ሰአት ያለቀ ነገር የለም። እስከመጨረሻው እንታገላለን ቡድናችንን አንድ ደረጃ ማድረስ አለብን በዬ አምናለሁ። የተሻለ ደረጃ ለመድረስ ከቀጣይ ጨዋታ ጀምሮ ቁርጠኝነታችንን  እናሳያለን ።