ጋና 2018 | ሉሲዎቹ አርብ ወደ አልጄርያ ይጓዛሉ

በጋና አስተናጋጅነት በ2018 ለሚደረገው ቶታል አፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ ሊብያን 15-0 በሆነ አጠቃላይ ውጤት በማሸነፍ ወደ መጨረሻው የማጣሪያ ዙር ማለፍ የቻለው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከአልጄሪያ ጋር ላለባቸው የመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታ ከነገ በስቲያ አርብ ወደ አልጀርስ ይበራሉ።

አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ  ዝግጅታቸውን ለአንድ ወር ያህል ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ሶስት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችንም ከተለያዩ የሀገር ውስጥ ቡድኖች ጋር አድርገዋል። መጠነኛ ጉዳት አጋጥሟት ለተወሰኑ ቀናት ልምምድ አቋርጣ የነበረችው የቡድኑ ወሳኝ አጥቂ ሎዛ አበራ አሁን ሙሉ ለሙሉ ከጉዳቷ አገግማ ልምምድ በመጀመሯ ወደ አልጄሪያ የመሄዷ ነገር እርግጥ ሲሆን በሌላ በኩል በልምምድ ወቅት ጉዳት ያስተናገደችው የደደቢቷ ተከላከይ መስከረም ካንኮ ጉዞ አጠራጣሪ ሆኗል።

ሉሲዎቹ ሁለት ቀን በሚፈጀው ጉዞ 18 ተጨዋቾችን በመያዝ በግብፅ በኩል ትራንዚት በማድረግ እሁድ አልጄሪያ የሚገቡ ሲሆን አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ወደ ስፍራው የሚያቀኑትን 18 ተጫዋቾች በጉዞው እለት አርብ ረፋድ ላይ ታሳውቃለች ተብሎ ይጠበቃል።

የፊታችን ረቡዕ ግንቦት 26 በአልጄሪያ የመጀመርያው የማጣርያ ጨዋታ የሚያደርጉት ሉሲዎቹ ጊዜው የረመዳን ጾም በመሆኑ በአልጄሪያ ሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ 4:00 ላይ አልጄሪያ ከፈረንሳይ ነፃ በወጣችበት ቀን (ጁላይ 5 1962) በተሰየመው ስታድየም የሚደረግ ይሆናል። የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ከአራት ቀናት በኋላ ሰኔ 3 እሁድ በአዲስ አበባ ስታድየም ሲደረግ በድምር ውጤት የሚያሸንፈው ቡድን የጋናው አፍሪካ ዋንጫን ትኬት የሚቆርጥ ይሆናል።