ኢትዮጵያ ቡና እና የቦባን ዝሪንቱሳ ጉዳይ…

ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ከውጪ ካመጣቸው ሁለት ተጫዋቾች መካከል አንዱን ከወር በፊት ማሰናበቱ ይታወሳል፡፡ ዩጋንዳዊው የአጥቂ አማካይ ቦባን ዝሪንቱሳ የተሰናበትኩበትን መንገድ ትክክል አይደለም በሚል ክለቡን ሲወቅስ ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በመመሪያው መሰረት ተጫዋቹን አሰናብቻለው የሚል ሃሳብ እየሰጠ ይገኛል፡፡

ለዛምቢያው ቢዩልዲኮን የተጫወተው ቦባን ወደ ኢትዮጵያ ያደረገው ዝውውር ስኬታማ አልነበረም፡፡ አንድም የነጥብ ጨዋታ ለኢትዮጵያ ቡና ያላደረገው አማካዩ ውሉ የፈረሰበትን መንገድ አሳማኝ አይደለም ሲል ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ “ከክለቡ ጋር ስምምነት ሳይኖረን ነው እንድለያይ የተደረጉት፡፡ ልምምድ ሜዳ ላይ ደብዳቤ አምጥተው ውልህ ፈርሷል አሉ፡፡ ከእኔ ጋር በውል መቋረጥ ዙሪያ ያደረግነው ድርድር የለም፡፡ ደሞዝም አልተከፈለኝም፡፡” ብሏል።

ቦባን አክሎም ጉዳዩን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከማሳወቅ ይልቅ ወደ ፊፋ ለመውሰድ እንደሚፈልግ አሳውቋል፡፡ “እኔ መብቴን የማውቅ ተጫዋች ነኝ፡፡ ለፌዴሬሽኑ ይህንን ማሳወቅ የለብኝም፤ ጉዳዩን እንዲዳኘን ለፊፋ ነው የማሳውቀው፡፡ በጉዳዩ ላይ ከወኪሌ ጋር መክሬ ለፊፋ ቅሬታዬን አሰማለሁ፡፡”

በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ቡና የቦርድ ፕሬዝደንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ለቦባን በልምምድ እና በወቅታዊ ብቃቱ ላይ ያለውን የተዳከመ እንቅስቃሴ እንዲያሻሽል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ “ተጫዋቹ በነበረው ጥሩ ያልሆነ ብቃት ምክንያት ሶስት ጊዜ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሰጥተነዋል፡፡ ሆኖም ደብዳቤዎቹን ለመቀበል እንኳን ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ በማስጠንቀቂያዎቹ ሊመለስ ስላልቻለ የመጨረሻ እርምጃ የነበረውን እና መመሪያው በሚፈቅድልን መሰረት ውሉን አፍርሰናል፡፡ ደሞዝ አልተከፈለኝም የሚለው ተቀባይነት የለውም፡፡ ውሉ እስከነበረ ድረስ የሚገባውን ክፍያ ፈፅመናል፤ ውል ከፈረሰ በኃላ ደሞዝ መክፈል አንችልም፡፡ ደሞዝ አልተከፈለኝም የሚለው ሃሳብ ፈፅሞ ሀሰት እና የማንቀበለው ነው፡፡” ሲሉ ሃሳባቸው ሰጥተዋል፡፡