የአስመራጭ እና ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች በአንድነት መግለጫ ሰጥተዋል

ለወራት ተጓቶ በመጨረሻም የፊታችን እሁድ ሠመራ ላይ እንደሚካሄድ የሚጠበቀውን ምርጫ የእስካሁኑ ሂደት አስመልክቶ ሁለቱ ኮሚቴዎች ሪፖርት ያቀረቡበት እና ጥያቄዎችን የመለሱበት መግለጫ ዛሬ 9 ሰዐት ላይ በቸርችል ሆቴል ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዘዳንት እና ስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ ሊካሄድ አንድ ቀን ብቻ ቀርቷታል። ሠመራ ላይ እየከተሙ በሚገኙት የክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እና የክለብ አመራሮች አማካይነት እንደሚደረግ የሚጠበቀው ምርጫ በአዲስ መልክ በተዋቀሩት የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አማካይነት እየተመራ ከምርጫው በፊት መሰራት የሚገባቸው ስራዎች ተጠናቀው ዛሬ ላይ ደርሰናል። ከረፋዱ 9፡00 ላይ በቸርችል ሆቴል የተጠራው መግለጫም ይህንኑ ሂደት የሚያስረዳ እና ከሚዲያ አካላት የተነሱ ጥያቄዎች የተመለሱበትም ነበር።

ፕሮግራሙ የጀመረው የአስመራጭ ኮሚቴው ያከናወናቸውን ተግባራት በዘረዘረበት ሪፖርት ነበር። የኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አስጨናቂ ለማ ኮሚቴው የምርጫውን መርሀ ግብት አሰናድቶ ከማሳወቅ ጀምሮ የመጨረሻዎቹን እጩዎች ይፋ እስከማድረግ ድረስ የነበሩትን ስራዎች በቅደም ተከተል እና የጊዜ ገደባቸውን በጠበቀ መልኩ ማከናወኑን በዝርዝር አስረድተዋል። በመቀጠል በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው በኩል ንግግር ያየረጉት ዋና ሰብሳቢው አቶ ሽፈራው አመኑ ደግሞ የቀረቡላቸውን ሶስት ቅሬታዎች የመረመሩበትን አግባብ አስረድተዋል። 

በዚህ መሰረት ኮሚቴው በአዲስአባባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፕሬዘዳንትነት በሚወዳደሩት ኢ/ር ፀደቀ ከፉክክር ውጪ መሆን ጉዳይ ላይ ያቀረበውን አቤቱታ ፌዴሬሽኑ የወካይነት ሚና የሌለው በመሆኑ እንዲሁም በተመሳሳይ መልኩ ከፉክክሩ የወጡት ኢ/ር ቾል ቤል ደግሞ ያቀረቡት አቤቱታ በተወሰነለት ጊዜ ውስጥ የቀረበ ባለመሆኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ውሳኔ እንዲፀና ማድረጋቸውን ገልፀዋል። በአንፃሩ በቃለ ጉባዬ የታገዘ ድጋፍ አላመጡም በተጨማሪም የትግራይ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ውክልናዬን አንስቻለው ብሏል በሚሉ ምክንያቶች ከምርጫው ውጪ እንዲሆኑ የተደረጉት አቶ ተስፋዬ ካህሳይ ላይ የተወሰነውን ውሳኔ መሻሩን አስታውቀዋል። የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ይህንን ያደረገውም በግለሰቡ እና በትግራይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሀከል የወካይ እና ተወካይ ግንኙነት ባለመኖሩ ፤ የቃለ ጉባኤ ጉዳይም በእግር ኳስ መተዳደሪያ ደንቡ ላይ ያልሰፈረ መስፈርት በመሆኑ እንደሆነ አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ኮሚቴዎቹ የምርጫ ደንቡ ያሉበት ድክመቶች እና የሚጣረሱ ሀሳቦች እንዲሁም ከግንዛቤ እጥረት የሚነሱ የመገናኛ ብዙሀኑ የአዘጋገብ ችግሮች ለስራቸው እንቅፋት እንደሆኑ እና በቀጣይ መታረም እንደሚገባቸው ገልፀዋል። ይህን ተከትሎም በስፍራው ከተገኙ የመገናኛ ብዙሀን ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ሲሆን በሚዲያ አካላት ላይ በሰነዘሩት ትችት ፣ በምርጫ ደንቡ ላይ አሉ ባሏቸው ክፍተቶች እና በክልሎች ድጋፍ ሰጪነት እና ውክልና መሀል ስላለው ልዩነት ሰፊ ክርክሮች ተደርገዋል።

አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ በበኩላቸው የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት በተሰጠው ሀላፊነት መሰረት የኮሚቴዎቹ ስራዎችን በመከታተል እና እገዛን በማድረግ ሂደቱን ሲያሳልጥ እንደቆየ ተናግረዋል። በመሆኑም ምርጫው ሚስተር ሱሊማን ዋቢሪ የካፍ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እንዲሁም የፊፋ ተወካይ የሆኑት ሚስተር ሉቃስ በተገኙበት በ145 ድምፅ ሰጪዎች እና በተለያየ የስራ አግባብ በሠመራ እነደሚገኙ የሚጠበቁ 212 ሰዎች ባሉበት እንዲካሄድ ሁሉም አይነት ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገው ማብቃታቸውን አስታውቀዋል።