ወልዋሎ ሁለት ተጫዋቾች አስፈረመ

በሊጉ ሁለተኛ የውድድር ዘመኑን ለመጀመር እየተዘጋጀ የሚገኘው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

ብርሀኑ ቦጋለ ከረጅም ጊዜያት የደደቢት ቆይታ በኋላ ለቆ ቢጫ ለባሾቹን ተቀላቅሏል። ብርሀኑ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በ1990ዎቹ መጨረሻ ወደ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ እስከ 2002 ቆይቶ ወደ ደደቢት አምርቷል። በሰማያዊዎቹ ቤትም ከ2006 ጀምሮ ቡድኑን በአምበልነት ሲመራ ቆይቷል።

ቢንያም ሲራጅ ሌላው ክለቡን የተቀላቀለ ተጫዋች ነው። አንጋፋው የመሀል ተከላካይ በሐረር ቢራ (አሁን ሐረር ሲቲ) ለረጅም ጊዜ ከቆየ በኋላ በ2007 ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አቅንቶ ቡድኑ እስከወረደበት 2009 ድረስ ቆይቷል። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ደግሞ በጅማ ቆይታ አድርጎ የሊግ ቻምፒዮን መሆን ችሏል። ተጫዋቹ በሐረር ቢራ እና ንግድ ባንክ አብሯቸው ከሰራው አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማርያም ጋር ለ3ኛ ጊዜ የሚገናኝ ይሆናል።

ክለቡ ከሁለቱ አዳዲስ ተጫዋቾች ፊርማ በተጨማሪ የ4 ተጫዋቾችን ኮንትራት ማደሱ የሚታወስ ነው።