ካፍ በሉሲዎቹ የተጫዋች ተገቢነት ክስ ላይ ምላሽ ሰጠ

ረቡዕ መስከረም 09 2011

በ2018 የጋና የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ በአልጄርያ ተሸንፎ ከውድድሩ የቀረው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በአልጄርያ ተጫዋቾች ላይ የተገቢነት ክስ መስርቶ ውሳኔ ሲጠብቅ መቆየቱ ይታወሳል። ካፍም ጉዳዩን ተመልክቶ የኢትዮጵያን ክስ ውድቅ ማድረጉን ለፌዴሬሽኑ ገልጿል። 

ፌዴሬሽኑ ለሚድያ የላከው ሙሉ መግለጫ ይህን ይመስላል:- 

ለካፍ የቀረበው የተጨዋቾች ተገቢነት ጥያቄ ምላሽ ተሰጠ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን /ሉሲዎቹ/ እ.ኤ.አ በ2018 በጋና አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከአልጄሪያ አቻቸው ጋር በአደረጉት ጨዋታ ወቅት የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ላይ የተጨዋች ተገቢነት ጥያቄ በተመለከተ ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ የመልስ ጨዋታቸውን ከሚያካሄዱበት ቀን አስቀድሞ ሁለት ተገቢነት የሌላቸው ተጨዋቾች የተመዘገቡ መሆናቸውን እና እነዚሁ ተጨዋቾች ቀደም ሲል ለዩናይትድ አረብ ኤምሬት የተጫወቱ እንደነበሩ ፤ በአሁኑ ወቅት ለአልጃሪያ ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት የተመዘገቡ መሆናቸው በመጥቀስ የተገቢነት ክስ ማቅረቡ ይታወሳል። የካፍ የዲስኘሊን ኮሚቴም ካይሮ ላይ በዋና ጽ/ቤቱ ሴኘቴምበር 8/2018 በአደረገው ስብሰባ ጉዳዩን በካፍ ደንብ እና በሴቶች የ2018 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የውድድር ደንብ መሠረት በመመርመር በካፍ የዲስኘሊን ኮድ መሠረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያቀረበውን ክስ ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በፌዴሬሽኑም በኩል በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ ይግባኝ ይጠይቃል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን