ዋልያዎቹ የቀይ መስቀል የዕድሜ ልክ አባል ሆነዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀይ መስቀል የዕድሜ ልክ አባል የሚያደርገውን ስምምነት ተፈራርሟል።

ረፋድ 4፡00 ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እና አምበሉ ጌታነህ ከበደ በካፒታል ሆቴል ከሰጡት መግለጫ በመቀጠል የቡድኑ አባላት በተገኙበት ሌላ መርሀ ግብርም ተካሂዷል። መርሀ ግብሩ ብሔራዊ ቡድኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ቦታ በመጠቀም ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያችለውን ስምምነት የፈፀመበት ነበር። አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱን ጨምሮ የኢትዮጵያ እና የአዲስ አበባ ቀይ መስቀል ማህበራት ኃላፊዎች በተገኙበት በዚሁ ዝግጅት የፌዴራሽኑ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ መስከረም ታደሰ ፣ የቡድኑ ምክትል አሰልጣኞች እና ተጨዋቾችም ታድመዋል።

ፕሮግራሙ የአዲስ አበባ ቀይ መስቀል የቦርድ ፕሬዘደንት የሆኑት ዶ/ር ሚልኬሳ ካባ ባደረጉት ንግግር የተጀመረ ነበር። ዶ/ር ምልኬሳ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር የቦርድ አባል የሆኑት አምባሳደር ዶ/ር ቶፊቅ አብዱራሂምን እና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ያላቸውን ግንኙነት ተጠቅመው መድረኩን በማዘጋጀታቸው አመስግነው ቀይ መስቀል በሀገራችን በሚከሰቱ ችግሮች ላይ ፈጥኖ ደራሽ መሆኑን እና በበጎ ፍቃድ ላይ ተመስርቶ የሚንቀሳቀስ ተቋም ስለመሆኑ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በመቀጠል የአዲስ አበባ ቀይ መስቀል ማህበር ጽ/ቤት ዋና ፀሀፊ የሆኑት አቶ አበባው በቀለ ለብሔራዊ ቡድኑ አባላት ስለ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ አመሠራረት ፣ ታሪክ እና አርማዎች ገለፃ አድርገዋል። ገለፃው የቀይ መስቀል እና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሰብዓዊነት ፣ ገለልተኝነት እና አለማቀፋዊነት መርሆቹ ከስፖርት ጋር ባለው መመሳሰል ዙሪያም ያተኮረ ነበር።

አቶ አበባው በተጨማሪ እንዳሉት የብሔራዊ ቡድኑ አባላት የቀይ መስቀል ዕድሜ ልክ አባል ሲሆኑ የማህበሩን መርሆች በዕለት ተዕለት ህይወታቸው የመተግበር ፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ላይ የመሳተፍ እንዲሁም ማህበሩን በገንዘብ እና በሀሳብ መደገፍ ይጠበቅባቸውል። በተቃራኒው ደግሞ ማህበሩ ለዋልያዎቹ በዓለምአቀፍ ደረጃ አንድ አይነት የሆነውን የአባልነት መታወቂያ እና እውቅና የመስጠት ፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እና የማህበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዲሳተፉ ማመቻቸት እንዲሁም የመጀመሪያ ዕርዳታ ስልጠናዎችን የመስጠት ኃላፊነት ይኖረዋል።

በመጨረሻም የብሔራዊ ቡድኑ አባላት የማህበሩ አባል የሚያደርጋቸውን መታወቂያ ፎርም የሞሉ ሲሆን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አበራ ቶላ ደግሞ የቀይ መስቀል አርማ ፒንን ለአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ፣ ለጌታነህ ከበደ እና ወ/ሮ መስከረም ከበደ ያበረከቱበት ሥነ ስርዓት ተካሂዶ የመዝጊያ ንግግሮች ከተደረጉ በኋላ የመርሀ ግብሩ ፍፃሜ ሆኗል።