የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ቅድመ ውድድር ዝግጅት | ቅዱስ ጊዮርጊስ

የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግጅትን የተመለከቱ መረጃዎች ላይ የሚያተኩረው ፅሁፋችን ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስመለክተናል።

የአስራ አራት ጊዜ የሊጉ ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮ በሀገር ውስጥ ውድድሮች ላይ ብቻ የሚሳተፍበትን የውድድር ዓመት ለመጀመር በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ከ2006 አንስቶ ለተከታታይ አራት ዓመታት የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ጊዮርጊስ አምና አምስተኛውን ለመድገም ያደረገው ጥረት እስከ 30ኛው ሳምንት ዘልቆ ሳይሳካ ቀርቷል። ከፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ ጋር በጀመረው የውድድር ዓመት ስድስት ተጫዋቾችን ከሀገር ውስጥ ቀሪ ሁለቱን ደግሞ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ወደ ቡድኑ ቀላቅሎ ነበር። ሆኖም በ2010 ያለ አሰልጣኝ ለውጥ የተረጋጋ ጊዜን ቢያሳልፍም በአፍሪካ ውድድሮችም ሆነ በፕሪምየር ሊጉ እና በኢትዮጵያ ዋንጫ ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል። ቡድኑ ምንም እንኳን ጥቂት ጨዋታዎችን (3) የተሸነፈ የሊጉ ክለብ ቢሆንም ነጥብ የጣለባቸው 13 ጨዋታዎች ዋጋ ያስከፈሉት ይመስላል። 14 ጨዋታዎችን በድል የተወጣው ጊዮርጊስ በሊጉ ከፍተኛውን የግብ መጠን (40) ማስቆጠር ቢችልም በአንፃሩ 19 ግቦችን አስተናግዶ በ21 የግብ ልዩነቶች በጅማ በሶስት ተበልጦ ዋንጫውን አጥቷል።


የውድድር ዓመቱ ከተጠናቀቀ በኋላ እንደ አብዛኞቹ ክለቦች ሁሉ ጊዮርጊስም ከበርካታ ተጫዋቾቹ ጋር ተለያይቷል። በዚህ መሰረትም ዘሪሁን ታደለ ፣ ደጉ ደበበ ፣ አበባው ቡታቆ ፣ አዳነ ግርማ ፣ ሮበርት ኦዱንካራ ፣ አብዱልከሪም ኒኪማ ፣ ኦዝቫልዶ ታቫሬዝ ፣ ሪቻርድ አፒያ እና አማራ ማሌ በፈረሰኞቹ ቤት የማንመለከታቸው ተጫዋቾች ሆነዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አምስቱ ከክለቡ ጋር ለረጅም ጊዜ የቆዩ በመሆናቸው የቡድኑን የመልበሻ ክፍል መንፈስ በብዙው የሚለውጠው እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም ቡድኑ በአዲሱ የውድድር ዓመት ሁሌም ጠንካራ ጎኑ ሆኖ የሚጠቀስለትን የአሸናፊነት ስነ ልቡና ለማስቀጠል ከቀሩት ነባር ተጫዋቾቹ ከሜዳ ላይ ብቃት ባሻገር የመሪነት ባህሪንም በእጅጉ ይፈልጋል። ረጅም ጊዜ አገልግለው ክለቡን ከለቀቁት ተጫዋቾች በተቃራኒ ደግሞ ወጣት ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ ተካተዋል። አምና ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ ይሰሩ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል ባህሩ ነጋሽ ወደ ዋናው ቡድን የሚያሳድገውን ውል የተፈራረመ ሲሆን ዮሃንስ ዘገየ እና ሳሙኤል ተስፋዬም በተመሳሳይ ሂደት ላይ ይገኛሉ። ሉክ ፖሊንሆ ፣ የዓብስራ ሙሉጌታ እና ቴዎድሮስ ገብረእግዚያብሔር ደግሞ ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ አድገው ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ እየሰሩ ነው።


በክረምቱ የዝውውር መስኮት ተሳትፎው ክለቡ በቁጥር የተመጠኑ ተጫዋቾችን አምጥቷል። ሂደቱም ሁሉም የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን የመተካት እና ሦስት ተጫዋቾችን ደግሞ ከሀገር ውስጥ የማስፈረም ነበር። ከሀገር ውስጥ ፈራሚዎች ውስጥ ሁለቱን አጥቂዎች አቤል ያለው እና ጌታነህ ከበደን ከደደቢት እንዲሁም የቀኝ መስመር ተከላካዩ ኄኖክ አዱኛን ከጅማ አባ ጅፋር ወደ ቡድኑ ተቀላቅለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ፓትሪክ ፓቴሲ (ኬኒያዊ ግብ ጠባቂ) ፣ ኢሴፉ ቦውራሀና (ቶጎዊ ተከላካይ) ፣ ካሲሞ ግሎቨር (ጋናዊ አማካይ) ፣ አሌክስ ኦሮቶማ (ናይጄሪያዊ አጥቂ) እና ኤድዋርድ ፍሪምፖንግ (ጋናዊ ተከላካይ) ከሀገር ውጪ ወደ ፈረሰኞቹ ቤት የገቡ ተጫዋቾች ሆነዋል። አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ ወደ ውጪ ተጫዋቾች አድልተው በተፈፀሙት ዝውውሮች ዙሪያ “የአምናው ውድድር እንዳለቀ ለቀጣዩ ምን እንደሚያስፈልገን የገለፅንበት ሪፖርት ነበር። ያለን ስብስብ ላይ በነበሩ ክፍተቶች ሦስት ተጫዋቾችን ከሀገር ውስጥ አስፈርመናል። ከዛ ውጪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሌም አራት ወይም አምስት የውጪ ተጫዋቾችን ስለሚጠቀም እና ሁሉም በመልቀቃቸውም ባለን በጀት እና በምንፈልገው የአጨዋወት ባህሪ ላይ ተመስርተን እነሱን ለመተካት አምስት ተጫዋቾችን አምጥተናል።” የሚለውን አስተያየት ሰጥተዋል።


የቅዱስ ጊዮርጊስ የቅድመ ውድድር ዝግጅት በነሀሴ ወር መገባደጃ ላይ በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ እግር ኳስ አካዳሚ ተጀምሯል። በመቀጠል ከመስከረም 11 ጀምሮ በሀዋሳ በተካሄደው የ2010ሩ የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ እና የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ተካፍሎ ዳግም ወደ አካዳሚው በመመለስ ከቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ እና ፋሲል ከነማ ጋር የተደረጉ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ጨምሮ በመደበኛ ዝግጅቱ ቀጥሏል። በልምምድ ላይ ካለው በስብስብ ውስጥ በብሔራዊ ቡድኑ የብሩንዲ ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ሳላሀዲን ባርጌቾ የሌለ ሲሆን መሀሪ መና ፣ አብዱልከሪም መሀመድ ፣ በሀይሉ አሰፋ ፣ ታደለ መንገሻ ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ሳሙኤል ተስፋዬ ከጉዳት አገግመው ቀለል ያሉ ልምምዶችን በመስራት ላይ ይገኛሉ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀደም ብለው ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት ከገቡ ክለቦች መካከል የሚጠቀስ ቢሆንም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ምክንያት በዝግጅቱ ጊዜያት ሙሉ ስብስቡን አለማግኘቱ እንዳስቸገረው አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ ይናገራሉ። “የቅድመ ውድድር ዝግጅታችን የተለመደው ዓይነት አልነበረም። ምክንያቱም የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ነበሩብን ወደ ብሔራዊ ቡድን የሄዱም ተጫዋቾች ነበሩ። በመሆኑም በዝግጅት ወቅት የተለያየ ግሩፕ እንዲኖረን እና መርሀ ግብራችንንም እንድንቀይር አድርጓል። አሁን ገና ነው ሙሉ ቡድኑን ማግኘት የቻልነው። ከውድድር በፊት ስድስት እስከ ሰባት ሳምንት ነው መስራት የነበረብን። ሆኖም ወደ ጥሎ ማለፉ የገባነው ከሦስት ሳምንታት ዝግጅት በኋላ ነበር። እሱንም ከብሔራዊ ቡድን የተመለሱ ተጫዋቾች በልምምድ ለአንድ ሳምንት ብቻ የተካፈሉበት ነበር። አሁን ከመጀመሪያው የሊግ ጨዋታ በፊት የዝግጃችን ጊዜ ከሰባት እስከ ስምንት ሳምንት ደርሷል። በብሔራዊ ቡድን በቂ የጨዋታ ደቂቃ ያላገኙ እና የተጎዱ ተጫዋቾችም ስላሉ አሁን ሁሉም ተመሳሳይ ደረጃ ላይ እንዲገኙ እየሰራን ነው። በጥቅሉ ግን ተጫዋቾች የሚሰጠውን የቅድመ ውድድር ስልጠና በጥሩ ሁኔታ እየተረዱ እንደሆነ አስባለው።”


የዝግጅት ጊዜያቸውን በጠቅላላው የቡድን መዋቅር ላይ በማተኮር እንደጀመሩ የሚናገሩት አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ አሁን ደግሞ በተናጠል ወደሚሰሩ እንደ የቆሙ ኳሶች አጠቃቀም ስራዎች ላይ ትኩረት እንዳደረጉ ይገልፃሉ። በዝግጅት ላይ የሚገኘው የቡድናቸውን ውህደት ሊደርሱበት ካሰቡት የመጨረሻ ግብ ጋር ሲያስተያዩት ያላቸውን ምዘና ደግሞ ” ሁሌም ቢሆን አሰልጣኝ በሁሉም ነገር ደስተኛ አይሆንም። ከተጫዋቾቹ ተጨማሪ የተሻሻለ ነገርን ማግኘት ይሻል። ብዙ መሻሻል የሚኖርበት ነገርም ይኖራል። በዋነኝነት በተለያዩ አቀራረቦች የሚጫወት ቡድን እንዲኖረን እንፈልጋለን። ለዛም የተለየ የአጨዋወት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ይዘናል።ስብስቡም ከአምናው የተሻለ ጥልቀት ያለው ነው። ለምሳሌ አምና በፊት መስመር ላይ ከአሜ ጉዳት ጋር ተጨምሮ የነበረብን ክፍተት አይኖርም። ሁሉም ቦታዎች ላይ በተመሳሳይ ወጣቶችም የተካተቱበት አማራጭ ይኖረናል። ” ሲሉ ያብራራሉ።

በ2010 የውድድር ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሚታወቅበት ቀጥተኛ አጨዋወቱ ወደ ኳስ ቁጥጥር ላይ መሰረት ያደረገ አጨዋወት እየተቀየረ መሆኑ አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል። ጉዳዩ ከአሰልጣኙ የጨዋታ ምርጫ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ዘንድሮም ተመሳሳዩን ሂደት ልንመለከት የምንችልበት ዕድል ሰፊ ነው። ” ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደማንኛውም ትልቅ ቡድን ጨዋታን ተቆጣጥሮ መጫወት ይኖርበታል። ያን ለማድረግ ደሞ ኳስን ተቆጣጥሮ የሚጫወት ቡድን ነው የምንገነባው ፤ ኳስን መያዝ ሳይቻል ጨዋታን መቆጣጠር ስለማይቻል። ከዛ ጎን ለጎን ግን የፊት መስመራችን ግቦችን በብዛት የሚያስቆጥር እንደሚሆን እናስባለን። በሁለቱም ሽግግሮች ላይም ፍጥነት እንዲኖረው ማድረግ ግባችን ነው።” የሚለው የፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ አስተያየት ይህንኑ የሚጠቁም ነው።


ቅዱስ ጊዮርጊስ የፕሪምየር ሊጉንም ሆነ የኢትዮጵያ ዋንጫን ማሸነፍ አለመቻሉ አይኖች በዋና አሰልጣኙ ላይ እንዲያርፉ አድርጓል። በቅርቡ ሊሰናበቱ የሚችሉበት ዕድል እንዳለም እየተነገረ ይገኛል። አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ ግን ትኩረታቸው ስለመጪው ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ። ” ጊዮርጊስን ይዤ በሊጉ የተሸነፍኩት ሦስት ጨዋታዎችን ብቻ ነው። ይህ ደሞ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር መጥፎ አይደለም ፤ ሊያውም በአጥቂ ስፍራ ላይ ከነበረብን ክፍተት አንፃር። የሊጉን ዋንጫ ለምን እንዳጣነው ደግሞ ሁሉም ሰው የሚያውቀው ነው። ጅማ ላይ የሆነውን መቼም የምረሳው አይደለም። በርግጥ የለፈው አልፏል አሁን ስለወደፊቱ ማሰብ እንደሆነ የሚገባን አውቃለው። አሁን ባለን ስብስብ ዕምነቴ ከፍ ያለ ነው። አምና ብዙ ነገሮች ለመቀየር ጥረት ላይ ነበርን። ቡድኑም ሽግግር ላይ ነበር። ዘንድሮ ትልቅ ተፅዕኖ የነበራቸው ተጫዋቾች ከመልቀቃቸው አንፃር ሽግግሩ ባይጠናቀቅም ከአምናው የተሻለ ደረጃ ላይ ነው። በእኔ እና በተጫዋቾች መሀከል እንዲሁም በምንሰራው ስራ መግባባት እና ዕምነቱ አለ። ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውም ጉዳይ የኔ የወደፊት ቆይታ ሳይሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ የወደፊት ሁኔታ ነው። ሆኖም እኔ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ችግር ነኝ ብዬ ካሰብኩ ቦርዱን ከማነጋገር እና ወደ ሌሎች ሀገሮች ሄጄ ስራዬን ከመቀጠል ወደ ኋላ አልልም። እዚህ ከመምጣቴ በፊት የሰራውትን አውቃለው ፤ እዚህም የሰራውትን አውቃለው። ስለዚህ የራሴ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አያሳስብኝም። አሁን ግን ትኩረቴ የቅዱስ ጊዮርጊስ መጪው ጊዜ ላይ ነው። ”

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ሲጀመር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህርዳር ከተማ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያደርገው ጥቅምት 25 ላይ ይሆናል።