ሪፖርት | መቐለ ደደቢትን ረቷል

የስያሜ እና የመቀመጫ ለውጥ ያደረጉትን መቐለ 70 እንደርታ እና ደደቢትን ያገናኘው ጨዋታ በመቐለ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

09፡00 ሰዓት ላይ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ያስጀመሩት የዕለቱ ጨዋታ በመቐለ 70 እንደርታ ሙሉ የጨዋታ ብልጫ የተወሰደበት ነበር። መቐለዎች በአዲስ ፈራሚዎቻቸው ዮናስ ገረመው እና ሳሙኤል ሳሊሶ ግቦች በመታገዝ የዓመቱ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታቸውን ያለችግር ማሸነፍ ችለዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአመዛኙ በፍጥነቱ ዝግ ያለ አጨዋወት የታየበት ቢሆንም በርካታ ሙከራዎች ተደርገውበታል። ከተጋጣሚያቸው አንፃር የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበራቸው መቐለዎች አሚኑ ነስሩ በሁለተኛው ደቂቃ ካደረገው ሙከራ በኋላ የፈጠሩት አጋጣሚ ወደ ግብነት ተለውጧል። አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመስመር ይዞ ገብቶ ያቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት የቀየረው ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው የመስመር አማካዩ ዮናስ ገረመው ነበር።

በጨዋታው የመቐለዎች ጫና በመፍጠር በደደቢት የሜዳ አጋማሽ ላይ መቆየት ተጋጣሚያቸው እንደልቡ ከሜዳው እንዳይወጣ እና ለስህተት እንዲዳረግ ምክንያት ሆኗል። የመስመር አማካዮቻቸው እና የአማኑኤል የተሳካ ጥምረትም የሜዳውን ስፋት ተጠቅሞ ደደቢትን ይበልጥ ለማስጨነቅ የረዳ ነበር። ከአማኑኤል ከመስመር የሚነሳ እንቅስቃሴ የተገኘ ሌላ አጋጣሚም ለጋብርኤል አህመድ አደገኛ አጋጣሚን ፈጥሮ ነበር። በፈጣን ሽግግር ሁለቱን የፊት አጥቂዎቻቸው አኩዌር ቻሞ እና እንዳለ ከበደን ለማግኘት ጥረት ያደርጉ የነበሩት ደደቢቶች ግን አብዲ ዳውድ ከርቀት አክርሮ ሞክሮ ፍሊፕ ኦቮኖ ካዳነበት አስደናቂ ሙከራ ውጪ ሌላ ዕድል መፍጠር አልቻሉም።

ከዕረፍት መልስ በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር የታየ ሲሆን በቁጥር ጥቂት ሙከራዎችም ተደርገዋል። በጨዋታው ኮከብ ሆኖ የዋለው አማኑኤል ከእረፍት መልስ ከጠባብ ማዕዘን አደገኛ ሙከራ ያደረገ ሲሆን በመቀጠለም በግሩም ሁኔታ ለሳሙኤል ሳሊሶ የግብ ዕድል ፈጥሮለት ነበር ፤ ሆኖም ሁለቱም ሙከራዎች በአዳነ ሙዳ ድንቅ ብቃት ጎል ከመሆን ድነዋል። መቐለዎች ያሬድ ብርሃኑን በዮናስ ገረመው ቀይረው ካስገቡ በኋላ መስመሮች ላይ የተሻለ ጥንካሬን ሲላበሱ በአንፃሩ መሀል ሜዳ ላይ የነበራቸው ብልጫ ቀንሶ ታይቷል። ያም ሆኖ 73ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ከሃይደር ሸረፋ የተላከችለት ግሩም ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ የቡድኑን መሪነት ማጠናከሩ አልቀረም። በቀሩት ደቂቃዎችም ባለሜዳዎቹ ሁለት ተጨማሪ ዕድሎችን የፈጠሩ ሲሆን ተዳክመው የታዩት ደደቢቶች ግን እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ያሬድ መሀመድ ከርቀት ካደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ ተጨማሪ አጋጣሚዎች ሳያገኙ ቀርተዋል። ጨዋታውም በመቐለ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሁለተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መቐለ 70 እንደርታ መቐለ ላይ ከወልዋሎ ዓ.ዩ ሲጫወት ደደቢት መቐለ ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናግዳል።


የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ይህን ይጫኑ | LINKማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ