የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-1 ባህር ዳር ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ዛሬ አዲስ አበባ እና ክልል ከተሞች ላይ ሲካሄድ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ወደ ሊጉ ያደገው ባህርዳር ከተማዎችን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አሰተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

“በተጫዋቾቼ ላይ ከፍተኛ የስነልቦና ስራዎችን በመስራታችን ይህን ውጤት ልናስመዘግብ ችለናል” ጳውሎስ ጌታቸው – ባህርዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው

“በዛሬው የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍተኛ ፈተና ሊገጥመን እንደሚችል ገምተን ነበር፤ ነገርግን በተጫዋቾቼ ላይ ከፍተኛ የስነልቦና ስራዎችን በመስራታችን ይህን ውጤት ልናስመዘግብ ችለናል ለዚህም ፈጣሪን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡”

“ፈጣን የመስመር ተጫዋቾችን እና መሀል ሜዳ ላይ ተክለ ሰውነትን ከቴክኒክ ክህሎት ጋር ያጣመሩ ተጫዋቾችን እንደመያዛችን በሜዳችን ሆነ ከሜዳ ውጪ እንደዛሬው አጥቅተን ለመጫወት እንሞክራለን፡፡”

“ከሲቲ ካፑ ስህተቶቻችን ተምረን የቆሙ ኳሶችን በተሻለ መንገድ ለመከላከል ሞክረናል። በዚህም የጊዮርጊሶችን ጥረት ማክሸፍ ችለናል፡፡”


“የቅንጅት ችግሮች ታይተውብናል” ዘሪሁን ሸንገታ -ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው መጥፎ የሚባል አልነበረም፤ የቻልነውን ያህል ጥረት አድርገናል፡፡ እግር ኳስ ይህ ነው፤ በአጋጣሚ በገባብን ጎል ተሸንፈን ልንወጣ ችለናል። በብሔራዊ ቡድን ጥሪ ምክንያት ብዙ ተጫዋቾች ሳንይዝ እንደመቆየታችን የቅንጅት ችግሮች ታይተውብናል፡፡”

ስለአዳዲስ ፈራሚ ተጫዋቾች

“የመጀመሪያ ጨዋታ እንደመሆኑ አንዳንድ የሚቀሯቸው ነገሮች ቢኖሩም ብዙም መጥፎ አይደለም፡፡”