ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ደቡብ ፖሊስ

ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ደቡብ ፖሊስን የሚያስተናግድበት የ6ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ የሚነሱ ዋና ዋና ነጥቦችን በዳሰሳችን እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።

ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ በማግኘት ደካማ ይመስል የነበረ አጀማመር ያደረገው ወላይታ ድቻ ከበድ ከሚሉት ተጋጣሚዎቹ መቐለ እና ቡና ያሳካቸው አራት ነጥቦች በሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ እንዲቀመጥ ረድተውታል። ሣምንት በአምስተኛው ሳምንት በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ ከአዲስ አበባ አንድ ነጥብ ይዞ መመለሱ ደግሞ የቡድኑን ተነሳሽነት ከፍ የሚያደርገው ነው። የነገ የድቻ ተጋጣሚ ደቡብ ፖሊስ ግን እስካሁን ከደካማው አጀማመሩ ማገገም አልቻለም። ሳምንት በፋሲል ከነማ በሜዳው የገጠመው ሽንፈትም ደደቢትን ከረታበት ጨዋታ ውጪ ሌላ ምንም ነጥብ ሳያገኝ የነበረበት ሦስት ነጥብ ላይ እንዲቀር ያስገደደው ነበር። በነገው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ድቻዎች ያሉበትን ጥሩ መንፈስ ለማስቀጠል ደቡብ ፖሊስ ደግሞ ቀጣዩን የሊግ ጉዞውን ለማቃናት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

ወላይታ ድቻ አምበሉ ተክሉ ታፈሰን እና ኄኖክ አርፊጮን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን ኃይማኖት ወርቁ እና እርቂይሁን ተስፋዬም ወደ ልምምድ የተመለሱ ቢሆንም ለነገው ጨዋታ አይደርሱም። በሌላ በኩል ለቡድኑ ጥሩ የሆነው ዜና የያሬድ ዳዊት እና ባዬ ገዛኸኝ ከጉዳት መመለስ ነው። በደቡብ ፖሊስ በኩል ደግሞ ጋናዊው ተከላካይ አዳሙ መሀመድ እና ደስታ ጊቻሞ በጉዳት የማይሰለፉ ሲሆን ግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ ግን ከነበረበት ጉዳት አገግሞ ለጨዋታው ብቁ ሆኗል፡፡

በጨዋታው ወደ ማጥቃቱ አመዝኖ የሚጫወት ወላይታ ድቻን እና ጥንቃቄን መሰረት አድርጎ የሚገባ ደቡብ ፖሊስ የማየት ዕድላችን የሰፋ ነው። በመሆኑም ከኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ በተለየ ድቻዎች የአማካይ ክፍል ተሳላፊዎቻቸው አመዛኙን ሰዓታቸውን በተጋጣሚ የሜዳ ክልል ላይ እንዲያሳልፉ የማድረግ ዕድል ይኖራቸዋል። እንደ እዮብ አለማየሁ እና ቸርነት ጉግሳ ያሉ የመስመር አማካዮችም ለብቸኛው የፊት አጥቂ ቀርበው እና የተጋጣሚያቸውን የመስመር ተከላካዮች ተጭነው እንደሚጫወቱ ይገመታል። በመሆኑም ደቡብ ፖሊሶች የአማካይ መስመራቸውን ለተከላካይ ክፍላቸው አስጠግተው ልፍተቶችን ለመዝጋት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የሚኖረው ትንቅንቅ የጨዋታውን ውጤት የመወሰን ዕድሉ የሰፋ ነው። ለፖሊሶች ወደ ሁለቱ አጥቂዎች የሚላኩ ቀጥተኛ ኳሶች ለመልሶ ማጥቃት ዕድል መፍጠሪያነት ጥቅም ላይ መዋላቸውም የሚቀር አይመስልም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ጨዋታው ሁለቱ ክለቦች እርስ በእርስ የሚገናኙበት የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ነው።

– ወላይታ ድቻ እስካሁን ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሁለቱ ግብ ሳይቆጠርበት የወጣ ሲሆን ጎል ማግባት የቻለውም በሁለት ጨዋታዎች ነው።

– ደቡብ ፖሊስ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ላይ ሁሉ ግብ ሲቆጠርበት ከአንድ በላይ ግብ የገባበት ግን በመከላከያ 2-1 በተረታበት ጨዋታ ብቻ ነው።

ዳኛ

– ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የሚመራው ዳንኤል ግርማይ ነው። ለዳንኤል በዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሀል ዳኝነት የተመደበበት ጨዋታም ነው።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

ታሪክ ጌትነት

እሸቱ መና – ዐወል አብደላ – ሙባረክ ሽኩር – ያሬድ ዳዊት

በረከት ወልዴ

ቸርነት ጉግሳ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ኄኖክ ኢሳያስ – እዮብ ዓለማየሁ

አንዱዓለም ንጉሴ

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

ፍሬው ገረመው

ዮናስ በርታ – ዘሪሁን አንሸቦ – ሳምሶን ሙሉጌታ – አበባው ቡታቆ

ብርሀኑ በቀለ – ኤርሚያስ በላይ – ሙሉዓለም ረጋሳ

መስፍን ኪዳኔ – በረከት ይስሃቅ – ብሩክ ኤልያስ