የአሰልጣኞች አስተያየት| ወልዋሎ 0-0 ድሬዳዋ ከተማ

በስድስተኛ ሳምንት የመጀመርያ ጨዋታ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ድሬዳዋ ከተማ ያለ ገየግብ በአቻ ውጤት ከተለያዩ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን በዚህ መልኩ ሰጥተዋል።

“የተጋጣሚያችን እንቅስቃሴ በመከላከል ላይ ያመዘነ በመሆኑ አስከፍተን ግብ ለማስቆጠር ተቸግረናል” ፀጋዬ ኪዳነማርያም

” የዛሬ ጨዋታ ጥሩ ነበር። ሆኖም የተጋጣሚያችን እንቅስቃሴ በጣም መከላከል ላይ ያመዘነ ነበር። በዚህም አስከፍተን ግብ ለማስቆጠር ተቸግረናል።
እንደ ተጋጣሚያችን ጥንካሬ ውጤቱ ጥሩ ነው። ነገር ግን እኛ ወደ ጨዋታው በደንብ ስንገባ እነሱ የጨዋታውን ፍጥነት ይቀንሱት ነበር፤ ጊዜም እያጠፉ ነበር። እኛ ማሸነፍ ቢገባንም ውጤቱ መጥፎ አይደለም። ተጫዋቾቼም የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል።

“የዚህ ቡድን አሰልጣኝ እኔ ነኝ። ተጫዋቾቼ ምን አይነት ብቃት አላቸው? በተቀያሪ ላይ እነ ማን አሉ? የሚለውን በደምብ አቃለው። ከኔ በላይ ማንም ሊያቃቸው አይችልም። ማንም ጥያቄ ስላነሳ ተጫዋችም አጨዋወት መቀየርም አልችልም።

” በዚህ ሰዓት ብዙ ቴክኒካል ችግሮች አሉብን። ዋንኛው ችግርም የተጫዋቾች ጉዳት ነው። ዋለልኝ ተጎድቷል፤ አስራትም ልምምድ ከጀመረ ብዙ ጊዜ አልሆነውም፤ አርባ የሚያክሉ ቀናት ጉዳት ላይ ነበር። በጨዋታው አብዱልራህማንን አስወጥተን በፕሪንስ ለማጥቃት ብንሞክርም የድሬዳዎች የመከላከል አደረጃጀት ሰብረን መግባት አልቻልንም።

አሰተያየት ትቀበላለህ። ግን ያሉህ የተጫዋቾች አማራጭ እና የምትፈልገው አጨዋወትም ይገድብሃል። ዞሮ ዞሮ ለቀጣይ ጨዋታ የአንድ ሳምንት ጊዜ ስላለን ክፍተቶቻችን አርመን እንቀርባለን። ”


“ጨዋታው ሚዛናዊ ነበር ፤ ሰላማዊም ነበር” አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ

” ጨዋታው ጥሩ ነበር። እኛ አስራ ስድስት ተጫዋቾች ይዘን ነው የመጣነው፤ ከነዛም ውስጥ በደምብ በጥሩ ሁኔታ ያላገገሙ ነበሩ። ካለን ስብስብ አንፃር ከሜዳችን ውጭ ጥሩ ውጤት ነው ይዘን የወጣነው። የተሻለ የማግባት እድልም ነበረብን፤ ግን አልተጠቀንባቸውም። በአጠቃላይ ጨዋታው ሚዛናዊ ነበር፤ ሰላማዊም ነበር። በዚህ አጋጣሚም በድሬዳዋ ከተማ ስም የትግራይ ህዝብን ማመስገን እፈልጋለው።

” ፕሪምየር ሊጉ በጣም የተዘበራረቀ ነው። እኛ ገና ሶስተኛ ጨዋታችን ነው፤ ስድስተኛ ሳምንት የደረሱም አሉ። ይህ ለኛ ጫና ይፈጥርብናል። እንደባለፈው ዓመት በሰባት ቀን ሶስት ጨዋታ ማድረግ ውስጥ እንዳንገባ ነው የምንሰጋው። እንደዛ ከሆነ ሁላችምም ውጤታችን ይበላሽብናል። ፌደሬሽኑ እነዚ ችግሮች እንዳይከሰቱ ቀሪ ጨዋታዎች ቶሎ ቶሎ ቢያጫውት ይሻላል እላለሁ። “