ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ መከላከያ

በስድስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ጎንደር ላይ ፋሲል መከላከያን የሚያስተናግድበትን ጨዋታ በሚከተለው መልኩ ዳሰነዋል።

በአፄ ፋሲለደስ ስታድየም 09፡00 ላይ የሚጀምረው ጨዋታ ፋሲል ከነማ መከላከያን ያስተናግዳል። በሲዳማ ተሸንፈው ዓመቱን የጀመሩት ፋሲሎች ከቀጣዮቹ ሦስት ጨዋታዎች የሰበሰቧቸው ሰባት ነጥቦች ደረጃቸውን ወደ ሦስት ከፍ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። በነዚህ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዳቸውም እየተጠናከሩ መምጣታቸውን የሚያሳይ ነው። ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ስንብት በኋላ ሳምንት በወልዋሎ ሽንፈት ለገጥመው መከላከያ ጨዋታው በመጀመሪያው ሳምንት ወደ ሀዋሳ ተጉዞ ደቡብ ፖሊስን ከረታ በኋላ የሚያደርገው ሁለተኛ የሜዳ ውጪ ጨዋታው ይሆናል። በመሆኑም በጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኙት አፄዎቹ ይበልጥ በደረጃ ሰንጠርዡ ከፍ ለማለት መከላከያ ደግሞ ከአህጉራዊው ውድድር ጀምሮ የሚታይበትን መቀዛቀዝ ለማስተካከል የሚገናኙበት ይሆናል።

የጎንደሩ ጨዋታ በዚህ ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች ሁሉ ጥቂት የጉዳት እና ቅጣት ዜናዎች የተሰሙበት ጨዋታ ነው። በዚህም ባለሜዳዎቹ ፋሲል ከነማዎች ጉዳት ላይ ከሚገኘው አጥቂያቸው ፋሲል አስማማው በቀር የሚያጡት ተጫዋች የሌለ ሲሆን በጦሩም በኩል የማይኖረው ቅጣት ላይ የሚገኘው ቴዎድሮስ ታፈሰ ብቻ ነው። ተመስገን ገብረኪዳን ደግሞ ከጉዳቱ ያገገመ የመከላከያ ተጫዋች ነው።

ጨዋታው በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድኖች መካከል የሚደረግ ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን አጫጭር ቅብብሎች የሚበራከትበት እንደሚሆን ይጠበቃል። የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን መውሰድ እና በነዚሁ የተመጠኑ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመግባት የሚደረግ ጥረትም እንዲሁ የጨዋታው አካል መሆኑ አይቀሬ ነው። በወልዋሎው ጨዋታ የተከላካይ መስመርን ማለፍ ተስኗቸው የነበሩት መከላከያዎች ከፋሲሎች አቀራረብ አንፃር የተሻለ ክፍተት ሊያገኙ በሚችሉበት በዚህ ጨዋታ ከማጥቃት አማካዮቻቸው ብዙ ይጠብቃሉ። በአንፃሩ ፋሲሎች የመሀል ሜዳ የበላይነታቸውን ማረጋገጥ ከቻሉ የመስመር አጥቂዎቻቸውን በዋናኝነት ወደ ጦሩ የግብ ክልል ለመግባት የመጠቀም አማራጫቸው የሰፋ ነው። በመሆኑም ይህ ቦታ አማካይ ክፍል ላይ ከሚኖረው ፍልሚያ ቀጥሎ ትኩረትን ይስባል። የተመስገን ከጉዳት መመለስ ደግሞ መከላከያ ላለበት ክፍተትን የመፍጠር ድክመት አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ለ5 ጊዜያት ተገናኝተው እኩል ሁለት ሁለት ጊዜ በመሸናነፍ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ በጨዋታዎቹ ፋሲል ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር መከላከያ አራት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል፡፡

– የመከላከያ ድሎች የተገኙት በ2000 በተደረገው የመጀመርያ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው እና በአምናው የመጨረሻ ጨዋታ በተመሳሳይ የ1-0 ውጤት ነው፡፡

– አምና ሁለቱም ክለቦች አንድ አንድ ጊዜ ድል ሲቀናቸው የጨዋታዎቹ ውጤቶች በተመሳሳይ 1-0 ነበሩ፡፡

 ዳኛ

– በሲዳማ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ መካከል በተደረገው ጨዋታ ዘጠኝ የማስቀቂያ ካርዶችን በማሳየት ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን የሰጠው ተፈሪ አለባቸው ይህን ጨዋታ ለመዳኘት ተመድቧል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሁሴን – ያሬድ ባየህ – ሙጂብ ቃሲም – አምሳሉ ጥላሁን

ሐብታሙ ተከስተ – ያስር ሙገርዋ – ኤፍሬም ዓለሙ

ሽመክት ጉግሳ – ኢዙ አዙካ – ሱራፌል ዳኛቸው

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

አቤል ማሞ

ሽመልስ ተገኝ – አዲሱ ተስፋዬ – አበበ ጥላሁን – ዓለምነህ ግርማ

በኃይሉ ግርማ

ሳሙኤል ታዬ – ዳዊት ማሞ

ፍሬው ሰለሞን

ተመስገን ገብረኪዳን – ምንይሉ ወንድሙ