ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ስሐል ሽረ ከ ሲዳማ ቡና

ሽረ ላይ ስሑል ሽረ እና ሲዳማ ቡና በሚያደርጉትን የነገ የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮችን በቅድመ ዳሰሳችን እንስመለክታችኋለን።

ሽረ እና ሲዳማ በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ በያዝነው ሳምንት የተገናኙበት ጨዋታ በፍፁም ቅጣት ምት ለመያየት አድርሷቸው በባለሜዳዎቹ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። ከሦስት ያለግብ ከተጠናቀቁ ጨዋታዎች በተገኙ ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሽረዎች በጥሎ ማለፉ ጨዋታ ሁለት ግቦችን ቢያስቆጥሩም የሊጉን የመጀመሪያ የሊግ ግባቸውን ለማግኘት ግን ገና በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን በሜዳቸው ድል ማድረግ የቻሉት ሲዳማዎች እስካሁን ሽንፈት ካላስተናገዱ አራት ቡድኖች መካከል ሲሆኑ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ጨዋታው በአዲስ ግደይ ምርጥ ብቃት ታግዘው በሊጉ ጥሩ ጅማሮ ላደረጉት ሲዳማዎች ሦስተኛ የሜዳ ውጪ ጨዋታ ፤ ከወዲሁ የመውረድ ስጋት ውስጥ እንዳይገቡ ለሚያሰጋቸው አዲስ አዳጊዎቹ ስሑል ሽረዎች ደግሞ በሜዳቸው የሚያደርጉት ሦስተኛ ጨዋታ ይሆናል።

ሸዊት ዮሃንስ ፣ ሀፍቶም ቢሰጠኝ እና ሠለሞን ገብረመድህን በጉዳት ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ የሱሑል ሽረ ተጫዋቾች ሲሆኑ ኢብራሒማ ፎፋናም የመግባቱ ነገር አጠራጣሪ ነው።  በሲዳማ ቡና በኩል ግን ምንም የቅጣትም ሆነ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን በአዳማው ጨዋታ በሁለትኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቶ ቅጣት ላይ የነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዋንጫው ጨዋታ የሁለቱ ቡድኖች ለዚህኛው ጨዋታ የሚረዱ ግብዓቶችን የሚያስጨብጥ መሆኑ ይታመናል። ምንም እንኳን የነገው ጨዋታ እንደ ትናንት በስትያው በርካታ ግቦች ይቆጠሩበታል ተብሎ ባይጠበቅም ክፍተት የሚኖረው ጨዋታ የመሆን ዕድል ይኖረዋል። የአጥቂ ባህሪ ባላቸው ተጫዋቾች የአማካይ ክፍላቸውን ግራ እና ቀኝ የሚያዋቅሩት ሽረዎች እነዚህን የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎች በሜዳው ቁመት ወደፊት ገፍተው ለማጥቃት እንደሚገቡ ይታመናል። ሆኖም ቡድኑ በብቸኝነት የሚጠመው የማጥቃት አማካይ ጅላሉ ሻፊ አጠቃላይ የማጥቃት ሂደቱ ለማሳለጥ ከተከላካይ አማካዩ ግርማ በቀለ ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል። የሀብታሙ መመለስ ይበልጥ የሚያጠነክራቸው ሲዳማዎች አሁንም ዋነኛ የማጥቃት አማራጫቸው አዲስ ግደይ መሆኑ ዕሙን ነው። በተለይም በጊዮርጊሱ ጨዋታ ላይ ደክሞ የታየው የሽረ የግራ ወገን የመከላከል ክፍል ለሲዳማዎች ወደ ቀኝ ያደላ ጥቃት ኢላማ መሆኑ የሚቀር አይመስልም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በኢትዮጵያ ዋንጫ ረቡዕ ዕለት ከተገናኙ በኋላ በታሪክ የሚያደርጉት የመጀመሪያ የሊግ የእርስ በእርስ ጨዋታ ነው።

– ስሑል ሽረ እስካሁን ባደረገው አራት የሊግ ጨዋታ ምንም ግብ ያላስቆጠረ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ግቦች ካስተናገደበት ጨዋታ ውጪ በሌሎቹ ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል።

– ሲዳማ ቡና እስካሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሙሉ ኳስ እና መረብ እያገናኘ ወጥቷል። በዛው መጠን በሁሉም ጨዋታዎች አንድ አንድ ግብ ተቆጥሮበታል።

– የሲዳማ ቡናው አጥቂ አዲስ ግደይ የሊጉን ከፍተኛ ግብ አግቢነት እየመራ ሲሆን በሁሉም ጨዋታዎች ላይ አንድ አንድ ግቦችን አስቆጥሯል።

ዳኛ

– በሰኞው የመከላከያ እና የወልዋሎ ጨዋታ ላይ አራተኛ ዳኛ ሆኖ የተመለከትነው ቢኒያም ወርቅአገኘው ይህን ጨዋታ በዋና ዳኝነት እንዲመራ ተመድቧል። ቢኒያም በሦስተኛው ሳምንት ሠባት የቢጫ እና አንድ የቀይ ካርድ ያሳየበት የሀዋሳ እና ወላይታ ድቻን ጨዋታ መዳኘቱ ይታወሳል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

ሙሉጌታ ዓንዶም – ዘላለም በረከት – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ሳሙኤል ተስፋዬ

ደሳለኝ ደባሽ – አሸናፊ እንዳለ

ሰዒድ ሁሴን – ጅላሎ ሻፊ – ኪዳኔ አሰፋ

ሚድ ፎፋና

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሣይ አያኖ

ዮናታን ፍሰሃ – ፈቱዲን ጀማል – ሰንደይ ሙቱኩ – ግሩም አሰፋ

ዮሴፍ ዮሀንስ – ግርማ በቀለ – ወንድሜነህ ዓይናለም

አዲስ ግደይ – ሀብታሙ ገዛኸኝ – ጫላ ተሺታ